Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመደመር ፍልስፍና በመመራት ለአየር ንብረት ተጽዕኖ ምላሽ እየተሰጠ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በመደመር ፍልስፍና በመመራት ለአየር ንብረት ተጽዕኖዎች ምላሾች እየተሰጠ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
የተባበሩት መንግሥታት አየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ 31) ‘ከቃላት ባለፈ ወደ ተግባርና አፈጻጸም መሸጋገር’ በሚል መሪ ሀሳብ በቱርኪዬ አንታሊያ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች ለማገገም ረጅም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ፣ ማህበረሰቡን በማስተባበርና አስቀድሞ በመንቀሳቀስ ዜጎች ያፈሩትን ንብረት የመጠበቅ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ፖሊሲ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአየር ንብረት ከድንበር የሚሻገር ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ የምታመርተው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ከውኃ የሚመነጭ መሆኑን ጠቁመው ይህም ለጎረቤት ሀገራት የሚላከውን የኃይል አቅርቦት ጭምር የሚያካትት መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የአረቢካ ቡና መገኛ ሀገር ብትሆንም፣ የሙቀት መጨመርና የዝናብ ስርጭት መዛባት ቡና የሚበቅልባቸውን ደኖችና ማሳዎች እየፈተኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ለእነዚህ ተጽዕኖዎች በመደመር ፍልስፍና በመመራት ምላሾች እየተሰጡ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
ፍልስፍናው ሰዎችን፣ ተቋማትንና ሀብቶችን በአንድ የጋራ ዓላማ ዙሪያ ለማሰባሰብ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም በየዓመቱ ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በችግኝ ተከላ የሚያደርጉትን ንቁ ተሳትፎ በአብነት ጠቅሰዋል።
በዚሁ የተቀናጀ ርብርብ እስካሁን ከ56 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ፣ የሀገሪቱ የደን ሽፋን እንዲሰፋና አረንጓዴ እንድትለብስ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ይህ ኢኒሼቲቭ የሥራ እድሎችን በመፍጠር የሕብረተሰቡን ኑሮ ከማሻሻሉም በላይ ዛፍ መትከል የዜጎች ባህል እንዲሆን ማድረጉን አመልክተዋል።
ከዚህ ባለፈም የተሰጠንን መሬት በማክበር፣ ከተፈጥሮ ጋር በስምምነት እንድንኖርና ለቀጣይ ትውልድ የምናወርሰውን ተፈጥሮአዊ ሀብት እንድንጠብቅ እያስተማረን ይገኛል ብለዋል።
ይህንን ሰፊ ሥራ ወደ ከተሞች በማስፋት የጎርፍ አደጋ መከላከያዎችን በመገንባት፣ የተበከሉ ወንዞችን በማጽዳትና የወንዝ ዳርቻዎችን ቤተሰቦች የሚሰባሰቡባቸው፣ ልጆች የሚጫወቱባቸው ፓርኮችና የእግር ጉዞ ማዘውተሪያዎች የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አብራርተዋል።
በዮናስ ጌትነት
Exit mobile version