አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡ ጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተከፍቷል፡፡
ይህ ጉባኤ የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ዋና ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ የአፍሪካውያን መሰባሰቢያ ማዕከልነቷን አረጋግጧል፡፡
እንዲህ ዓይነት ጉባኤዎች ከተለመደው ስብሰባ የላቀ ፋይዳ አላቸው፡፡ ዛሬ ጠዋት ብቻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከሴራሊዮን ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ማዳ ቢዮ፣ ከቡሩንዲ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ኤቫሪስት ንዳይሺማዬ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼክ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን እንዲሁም ከዩጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄሲካ አልፖ ጋር ተወያይተዋል።
እነዚህ ውይይቶች የሁለትዮሽና የቀጣናዊ ግንኙነትን ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ትብብርን ለማስፋት እና የኢትዮጵያን አቋም ለማስረዳት ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራሉ፡፡ በአንድ ቦታ በርካታ መሪዎችንና ባለድርሻ አካላትን ማግኘት ደግሞ በተናጠል ጉብኝት ሊገኝ የማይችል ጊዜና ወጪ ቆጣቢነት አለው፡፡
“የአፍሪካ የጤና ደህንነትና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ የጀመረው 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ትልቅ ትርጉም ያለው መድረክ ነው።
የጉባኤው መሪ ሀሳብ ከኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫ ጋር የተጣጣመ ሲሆን፤ ከጥገኝነት ወደ ባለቤትነት መሸጋገር ማለት አፍሪካ መድኃኒትና ክትባት በራሷ እንድታመርት፣ የጤና ሥርዓቷን በራሷ አቅም እንድትገነባና ለወረርሽኝ አስቀድማ እንድትዘጋጅ ማድረግ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም፣ በባለሙያዎች ሥልጠናና በመድኃኒት ምርት ያካበተችውን ልምድ የምታካፍልበት፣ ከአጋሮቿ ደግሞ ኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ የምትስብበት መድረክ ይሆናል፡፡ ይህም ብሔራዊ ጥቅሟንም ያሳካል፡፡
አዲስ አበባ በርካታ ጉባኤዎችን በብቃት የምታስተናግድ ከተማ ናት። ይህ ብቃት ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ አጀንዳ በመቅረጽ ረገድ ያላትን ተሰሚነት ያሳድጋል፡፡ ይህ ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት ደግሞ ብሔራዊ ጥቅምን ለማሳካት ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
ከዚህ አለፍ ሲልም የሆቴል፣ የትራንስፖርት፣ የቱሪዝምና የአገልግሎት ዘርፎች ከተሳታፊዎች ፍሰት ተጠቃሚ ይሆናሉ፤ የውጭ ምንዛሪም ይገኛል፡፡ ከቡና በጀበና እስከ ትላልቅ ሆቴሎችም ይነቃሉ፣ ይነቃቃሉ፡፡
ኢትዮጵያ ግዙፉን 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ32) ለማስተናገድ ዋዜማ ላይ ደርሳለች።
ኮፕ32 ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ በታዳሽ ኃይል ልማትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ስርዓት በመዘርጋት ያስመዘገበችውን ውጤት ለዓለም የምታሳይበት፣ የአፍሪካን የአየር ንብረት ፍትሕ ጥያቄና የፋይናንስ ፍላጎት የምታስተጋባበትን እድል ይፈጥራል።
ይህም የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ ገጽታ ከመገንባት ባሻገር የአየር ንብረት ፋይናንስና ቴክኖሎጂ ድጋፍ ለማግኘት ያስችላል፡፡
ዛሬ በመዲናዋ እየተስተናገደ የሚገኘው ጉባኤ ላይ ከመሪዎች ጋር የተደረጉት ውይይቶች እንደሚያሳዩት፣ አዲስ አበባ ለአህጉሪቱ የውይይትና የውሳኔ መድረክ ብቻ ሳትሆን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መሳካት ወሳኝ እየሆነች መምጣቷን ነው፡፡
ተከታታይ ጉባኤዎችን በብቃት መምራትና ውጤታቸውን ወደ ተጨባጭ ሀገራዊ ጥቅም መቀየር ደግሞ ከፊታችን የሚጠብቀን ዋነኛ ተግባር ነው፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በአፈወርቅ እያዩ

