አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ሲከናወን በቆየው የኢኮኖሚ ሪፎርም ሥራ ምክንያት ፈተናዎችን የሚቋቋም አቻዮ የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት ችለናል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
7ኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳው ጥያቄና አስተያየት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ እንዳሉት፤ ባለፉት 11 ዓመታት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ክለሳ ተካሄዶ አያውቅም።
በመሆኑም አዳዲስ የተጨመሩ ኢኮኖሚዎችን ለማካተትና ሚና የሌላቸውን የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለማስወጣት ባለፈው አንድ ዓመት ከፍተኛ የሰው ኃይል በማሰማራት የኢኮኖሚ ክለሳ ሲካሄድ ቆይቷል ብለዋል።
ከዚህ በፊት በኢኮኖሚ ያልተካተቱ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ የኮሪደር ልማት፣ ክላስተር ግብርና፣ ሌማት ትሩፋት፣ ተጨማሪ ኢንዱስሪ ፓርክ ፣ አረንጓዴ ዐሻራ፣ አዳዲስ የኢነርጂ ፕሮጀክቶችን የሚለካ ሥርዓት እንዳልነበረ አስታውሰዋል።
በተጨማሪም ኮንፈረንስ ቱሪዝም፣ የቱሪዝም መሰረተ ልማት፣ ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎችን የሚለካ ሥርዓት እንዳልነበረ ጠቅሰው፤ ክለሳው እነዚህንና ሌሎችን በማካተት ተሰርቷል ብለዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት በተቀመጡ መመዘኛዎች 210 ቢሊየን ዶላር በመሆን ከሰሃራ በታች ከደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ቀጥሎ ሶስተኛው ኢኮኖሚ ሆኗል ነው ያሉት።

