Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሀገራዊ ምክክሩ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦች እንዲተገበሩ መንግሥት ጽኑ አቋም አለው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ለአራት ዓመታት የተለፋባቸው ምክረ ሐሳቦች በሕግ፣ በፖሊሲና በአስተዳደር ተግባር ላይ እንዲውሉ መንግሥት ጽኑ አቋም አለው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በ7ኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በመሰባሰብ ስለ ሀገራቸው ጉዳዮች በጋራ እንዲመክሩ ዕድል የፈጠረ ታላቅ ስኬት ነው።

ላለፉት አራት ዓመታት በሀገር ውስጥና በውጭ ከመቶ ሺህ በላይ ዜጎች በምክክር ሂደቱ መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩና የተለያዩ እምነቶችን የሚከተሉ ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት ያነሱበት መድረክ መሆኑን አብራርተዋል።

ከአራት ዓመታት የውይይት ሂደት በኋላ 4 ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎች ለ46 ቀናት በአንድ አዳራሽ በመሰባሰብ መክረዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ውስብስብ የሆነውን ሂደት በትዕግሥትና በኃላፊነት በመምራት ውጤቱን አደራጅተው ምክረ ሐሳቦችን በስኬት ማቅረባቸውን አድንቀዋል።

የውይይቱ ውጤቶች በተለያዩ መንገዶች መፍትሔ የሚያገኙ መሆናቸውን በማብራራት፤ አንዳንዶቹ በፖሊሲ፣ ሌሎቹ በአስተዳደራዊ እርምጃ፣ የተወሰኑት ደግሞ በሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮች እንደሆኑ ገልጸዋል።

በመደመር ግራንድ ስትራቴጂም ውስጥ ከብሔራዊ ምክክክሩ የተገኙ ምክረ ሐሳቦችን እንዲካተቱ መደረጉን አስረድተዋል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version