Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፡ የአፍሪካ አቪዬሽን መልህቅ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሪ ቃሉ “አዲሱ የአፍሪካ መንፈስ” የሚል መሆኑ የተቋሙን አህጉራዊ አስተዋጽኦ በትክክል ይገልጻል።

 

የስታር አልያንስ አባል የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበርካታ ተግዳሮት ውስጥ አልፎ እያካሄደ የሚገኘው መጠነ ሰፊ የማስፋፊያና የማዘመን ጉዞ የአንድ ብሔራዊ አየር መንገድ እድገት ብቻ ሳይሆን፣ የመላው አፍሪካን የአቪዬሽን ምህዳር ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ወሳኝ ተቋም ነው።

 

የ80 ዓመቱ አየር መንገድ ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ካሉ የአቪዬሽን ማዕከል አንዷ ለማድረግ ሜጋ የግንባታ እና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን እያካሄደ ነው፡፡ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ በ12 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ወጪ ግንባታው የተጀመረው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

 

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን የመያዝ አቅም እየተፈታተነ ላለው መንገዶኞች የማስተናገድ አቅም መፍትሄ ነው፡፡

 

የመጀመሪያው ምዕራፍ በ2030 ሲጠናቀቅ በዓመት 60 ሚሊየን መንገደኞችንና 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም የሚኖረው አውሮፕላን ማረፊያው፤ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 110 ሚሊየን መንገደኞችን በመቀበል የአፍሪካ ትልቁና ከመካከለኛው ምስራቅ የአቪዬሽን ማዕከላት ጋር የሚፎካከር ግዙፍ መናኸሪያ ይሆናል።

 

ይህ የመሰረተ ልማት ግንባታ በዘመናዊ አውሮፕላኖች ግዢና በቴክኖሎጂ ሽግግር የተደገፈ ሲሆን ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራትም በአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲው አማካኝነት ያሰለጥናል፡፡

 

እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ለመግዛት በግዢ ሂደት ላይ ሲሆን፤ አየር መንገዱ ባጠቃላይ ከ65 በላይ የአፍሪካ ከተሞችን ጨምሮ 150 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በማገናኘት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እና የአንድ አፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ (SAATM) እውን ለማድረግ እየሰራ ነው።

 

ከበረራ ባሻገር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፕላን ጥገና እና በአቪዬሽን አካዳሚው በኩል የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ባለሙያዎችን በማሰልጠንና ለቀጠናው አየር መንገዶች የጥገና አገልግሎት በመስጠት አህጉሪቱ ከውጭ ጥገኝነት እንድትላቀቅ አዲስ መንፈስ እየፈጠረ ነው።

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘንድሮ የ2027 አፔክስ (APEX) ባለአምስት ኮከብ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች አንዱ እንዲሁም በአፍሪካ የአፔክስ ምርጥ  አየር መንገድ በመሆን እውቅና ተሰጥቶታል፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ እና በቀጣናው በአቪዬሽን ሥልጠና፣ በሰው ሀብት ልማት ግንባታና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት በማቅረብ በ58ኛው የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ ላይ የላቀ አገልግሎት ሽልማት አግኝቷል።

 

በካርጎ እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በ2026 በተካሄደው የአረቢያን ካርጎ ሽልማት ላይ ለተከታታይ አራተኛ ጊዜ የአፍሪካ ምርጥ የካርጎ አየር መንገድ በመባልም ተሸልሟል።

 

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ምክር ቤት መመረጧ የዘርፉን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ያረጋግጣል።

 

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት አፍሪካ በራሷ አቅም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ መገንባት እንደምትችል በተጨባጭ ያሳያል።

 

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

 

በቴዎድሮስ ሳህለ

Exit mobile version