Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል ሰላም መስፈን አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ሰላም መስፈን አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና የመስጠት ስነ ስርዓት ተከናወነ።
 
“ለዘላቂ ልማትና አብሮነት የህግ የበላይነት” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው ስነ ስርዓት የፌዴራል እና የክልሎች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
 
በስነ ስርዓቱ ላይ የአማራ ከልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ባደረጉት ንግግር በክልሉ ጠንካራ አመራር በመስጠት የፀጥታ መዋቅሩን በማስተካከል እና ህዝቡን በየደረጃው በማወያየት ለህግ መከበር እና ለሰላም መስፈን ዘብ እንዲቆም ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።
 
ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ህገ ወጦችን በቁጥጥር ስር የማዋል እና ቀስ በቀስ ክልሉን ከነበረበት የሰላም መደፍረስ እንዲወጣ ማድረግ ተችሏል ሲሉ አንስተዋል።
 
አሁን ለመጣው ሰላም የጎላ ሚና ለነበራቸው እና አጠቃላይ ከክልሉ ለተውጣጡ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለሃገር ሽማግሌዎች፣ ለወጣቶችና ለጸጥታ አካላት የእውቅና መሥጠት ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል።
 
በስነ ስርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የኢፌዴሪ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም አደም መሀመድ፣ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፣ የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
 
በአጠቃላይ ለክልሉ ሠላም መምጣት ጉልህ አስተዋፅኦ ላደረጉ 150 ግለሰቦች፣ ለክልሉና ለፌደራል ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።
 
ስነ ስርዓቱ በክልሉ ርዕስ መስተዳድርና በክልሉ ሠላምና ደህንነት ግንባታ ቢሮ በጋራ የተዘጋጀ የሠላም ምስጋና ዕውቅና ፕሮግራም ነው።
 
በናትናኤል ጥጋቡ
Exit mobile version