አዲስ አበባ ፣ዻጉሜ 5 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለፀጥታ ሲባል በአዲስ አበባ ማንኛውም ግለሰብ ርችት መተኮስ እንደማይችል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት የሚዲያ ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሰጡት መግለጫ÷ ርችትን ምክንያት በማድረግ የሽብር ጥቃት ለማድረስ እየተዘጋጁ ያሉ ግለሰቦች መኖራቸውን ፖሊስ በጥናት ደርሶበታል ብለዋል።
ስለሆነም ወንጀልን ለመከላከል አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ማንኛውም ግለሰብ ርችት መተኮስ አይችልም ብለዋል። ይህንን ተላልፎ ርችት የሚተኩስ ማንኛውም ሰው በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚውልም ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜናም በአዲስ አበባ በአስሩም ክፍለ ከተማ በጥናት በተደረገ ፍተሻ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል።
በፍተሻው አንድ ቦምብ እና አራት ሽጉጦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው የተናገሩት።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም የተጠረጠሩ 180 ግለሰቦች ተይዘው ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።
ዋና ኢንስፔክትር ማርቆስ አያይዘውም ህብረተሰቡ የራሱን ሰላም በመጠበቅ፣ ሰላምን ሊያውኩ የሚችሉ ወንጀለኞችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል።
በመሰረት ደምሱ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

