Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤና የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅታዊ፣ ሀገራዊና ከተማ አቀፍ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አበባ ከአስሩም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያዩ።

በውይይቱ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ፣የአዲስ አበባ ብልፅግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ እንዲሁም የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

ውይይቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው የለውጥ ጉዞ የተመዘገቡ ስኬቶች እና የነበሩ ፈተናዎች እንዲሁም አሁናዊ ሁኔታዎችን መገምገማቸው ተጠቅሷል።

በውይይቱ ላይ ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ ለወሰዳቸው እርምጃዎች ያላቸውን አድንቆት ገልጸዋል፡፡

በቀጣይነትም የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ ፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሊሰሩ በታቀዱ ስራዎች ዙሪያ ያላቸውን ጥያቄ ለወይዘሮ አዳነች አቅርበዋል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ ነዋሪዎች ሰላምና ጸጥታን ማረጋገጥ፣ የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ህገወጥ ተግባራትን አስቀድሞ በመከላከል እና ህገወጥ የመሬት ወረራን በመመከት የበኩሉን ተሳትፎ ማድረግ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩም ከህብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን እና ጥቆማዎችን በአግባቡ በመፈተሸ ለብልሹ አሰራሮች እና ስርዓት አልበኝነት ምክንያት የሆኑ አካላት ተጠያቂ ለማድረግ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በከተማ ደረጃ ባለፉት ሁለት ዓመታት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰራው ስራ የህብረተሰቡን ኑሮ በሚታይ መልኩ የሚለውጡ በርካታ ስራዎች መሠራታቸውን ነዋሪዎቹ አንስተዋል።

ምክትል ከንቲባዋም በመዲናዋ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች የነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ባለፈ የከተማዋን ገጽታ በመለወጥ በኩል ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

በተጨማሪም በመዲናዋ በድምቀት የሚከበሩት የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላትን ነዋሪው ራሱን ከኮቪድ-19 ወረርሽን በመከላከል እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version