Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ጋር ተወያዩ፡፡

በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ በርካታ ተስፋዎችን መሰነቋን ጠቅሰው የህዳሴ ግድብ ውጤታማ ክንውን እንዲሁም በኮሮና ቫይረስ እየተፈተነም ቢሆን የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ማደጉ ትልቅ ተስፋ መሆኑን ገልጸዋል።

በእነዚህ ውጤታማ እንቅስቃሴዎች እየተጓዝን ቢሆንም አልፎ አልፎ ችግሮች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

ሆኖም እነዚህ ችግሮች ኢትዮጵያ ለማሳካት የጀመረቻቸውን ትልሞች አያደናቅፉምም ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የእርቀ ሰላም ኮሚሽን እስካሁን ያደረጋቸውን ጥረቶች በማድነቅም በቀጣይ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ ለመሆን እንዲሰራም ጠይቀዋል።

መንግስትም የኮሚሽኑን መልካም ጅምሮች ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው፤ ኮሚሽኑም ያለውን አቅም ለማጎልበት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ በበኩላቸው ኮሚሽኑ እስካሁን ስላከናወናቸው ተግባራት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት ስትራቴጂክ እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን አምስት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ማደራጀቱንም ገልጸዋል።

ከቋሚ ኮሚቴው መካከል ሶስቱ የኮሚሽኑን ዋና ዋና ተግባራት የሚያከናውኑ እንደሆኑ መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version