አዲስ አበባ ፣ መስከረም 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) 2ኛው የኢሬቻ የሰላም ፎረም በሸራተን አዲስ እየተካሄደ ነው።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ኦሮሞ ወደ ቀደመ ማንነትና እሴቶቹ እንዲመለስ የክልሉ መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ወንድማማችነትን ማጠናከር እና ነፃነትን ማረጋገጥ እጅጉን አስፈላጊ ነው ብለዋል አቶ ሽመልስ።
የገዳ ስርአትን በትምህርት ስርአቱ ውስጥ ለማካተት የተደረገውን ጥረት ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ገዳ የሁሉም የህይወት አካል እንዲሆን በተግባር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው በቀጣይ አመት በተሻለ እና ባማረ ሁኔታ እናከብር ዘንድ ዘንድሮን በጥንቃቄ ማሳለፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢሬቻን በዓል በተሻለ ለማስተዋወቅ እና ግንዛቤ ለመፍጠር እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርስነት ለማስመዝገብ ዓለም አቀፍ እና ሃገር አቀፍ ፎረሞች እንደሚካሄዱም በመድረኩ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት የሚካሄድባቸው ይሆናል፡፡
በፎረሙ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የተለያዩ ሃገራት ዲፕሎማቶች፣ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ የዩኔስኮ ተወካዮች፣ አባ ገዳዎችን ጨምሮ 250 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የገዳ ስርአት 2009 ዓ.ም አዲስ አበባ በተካሄደው 11ኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ ላይ በቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል፡፡
በሀብታሙ ተክለስላሴ

