Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፋና ቴሌቪዥን የአረብኛ ቋንቋ ስርጭት በይፋ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በአረብኛ ቋንቋ የሚያስተላልፋቸውን ዝግጅቶች ዛሬ በይፋ ጀመረ።

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክም የራሱን ቀለምና አሻራ እያሳረፈ የዘለቀው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት 25ኛ ዓመቱን እያከበረ ባለበት ወቅት ነው በቴሌቪዥን ዘርፍ በአረብኛ ቋንቋ ዝግጅቶችን በዛሬው እለት ማስተላለፍ ጀምሯል።

ዝግጅቶቹ ከሰኞ እስከ አርብ ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ለአንድ ሰዓት ያክል በአረብኛ ቋንቋ ለተመልካች የሚያቀርብ ሲሆን የመጀመሪያ ስርጭቱንም ዛሬ ለተመልካቾች ማቅረብ አቅርቧል።

ስርጭቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽነር እና የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዲሁም የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በይፋ አስጀምረውታል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው÷ ከባህል ትስስሩ ባሻገር ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስራ የአረብኛ ቋንቋ መጀመሩ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

እንዲሁም ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ለኢትዮጵያ ቅርብ የሆኑት የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የበለፀጉ መሆናቸው ከሀገራቱ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያስችላልም ነው ያሉት።

በተጨማሪም ከቱሪዝም አንፃር ጎብኚዎችን ለመሳብ ፣ በግብርናው እና በማዕድን ዘርፉ የአረብኛ ቋንቋ ወሳኝ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽነር እና የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው የኢትዮጵያን ባህል፣ ቋንቋ እና ማህበራዊ መስተጋብር ለማስተዋወቅ ሚዲያ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን በማወቅ የአረብኛ ቋንቋ መጀመሩን ገልፀል።

ተቋሙ የአረብኛ ቋንቋን ሲጀምር ኢንቨስትመንትን መሳብ፣ ባህልን ማስተዋወቅና በንግድ መተሳሰርን አላማ በማድረግ ነው ብለዋል አቶ ንጉሱ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፋና ከአመሰራረት ጀምሮ ያለፈበት ሂደት ለሁሉም ማህበራዊ ትምህርት እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

ኢንቨስትመንትን፣ ንግድን እና ቴክኖሎጂን ለማምጣት እና አብሮ ለማደግ እንዲሁም ለመበልፀግ የአረብኛ ቋንቋ መጀመር አስፈላጊ መሆኑን በመግለፅ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለዚህ የዲፕሎማሲ ስራ ፋና ወጊ ሆኗልም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።

የአረብኛ ቋንቋ ከህዳሴ ግድብ ጋር ካለው የዲፕሎማሲ ሚና ባሻገር ከግድቡ መጠናቀቅ በኋላ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም ወሳኝ እንደሆነም አብራርተዋል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ባደረጉት ንግግር የአረብኛ ቋንቋ መጀመሩ የኢትዮጵያን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እውን ለማድረግ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

ከዚህ ባለፈም በተለያዩ አረብ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን መረጃ ፍላጎት ሟሟላት ዓላማ ያደረገ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

አያይዘውም የስርጭቱ መጀመር ከጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነም አንስተዋል።

ለስርጭቱ በጥናት ላይ የተመሰረቱ ዝግጅቶች ሲከናወኑ መቆየታቸውን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰጠኝ እንግዳው አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ የምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና እና አካባቢያዊ ሁኔታ በአረብኛ ቋንቋ የተለያየ ይዘት ያላቸውን ዝግጅቶች ማስተላለፍ የጀመረበት አንዱ ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ እና በአጠቃላይ በአባይ ተፋሰስ ፍትሃዊ አጠቃቀም ላይ ውዝግቦች እና ክርክሮች መነሳታቸው የሚታወቅ ሲሆን በአረብኛ ቋንቋ የሚናገሩ እና በተለያየ ምክንያት ከኢትዮጵያ በተቃራኒ ማዕዘን ላይ የቆሙትን ሁሉ ትክክለኛ መረጃ በማድረስ የኢትዮጵያን አቋም ለመስረዳት የሚቻልበት መንገድ መፍጠርም ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡

በተጨማሪም ከተከለሰው ሃገራዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር የሚናበቡ ስራዎችን ማከናወን፣ የኢትዮጵያን ባህል ለዓረቡ ዓለም ሃገራት ማስተዋወቅ፣ ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ ከአረብ ሀገራት ጋር ባህላዊ እና ማህበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስር ማጠናከር የጅማሬው ግብ ሆነው ተቀምጠዋል።

ስርጭቱ እንዲጀመር መላው የፋና ሰራተኞች፣ የቦርድ አባላት እና ሌሎች በአረብና ቋንቋ ቀድመው ስርጭት የጀመሩ ሚዲያዎችም ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር የጠቀሱት የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከዚህ ቀደም በድረ ገፅ እና የተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆችን በመጠቀም በአረብኛ ቋንቋ ተከታዮቹ ዘንድ ሲደርስ መቆየቱም ይታወቃል።

በቴሌቪዥን መስኮትም ከአማርኛ በተጨማሪ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ አድማጭ ተመልካቾቹ ዘንድ መድረስ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል።

በሬዲዮ ዘርፍም በብሄራዊ ስርጭት እና በመላው ኢትዮጵያ 12 የኤፍ̣.ኤም ጣቢያዎች ያቋቋመ ሲሆን፥ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ አፋርኛ፣ ሶማሊኛ፣ ትግርኛ፣ ወላይትኛ እና ሲዳምኛ የስርጭት ቋንቋዎቹ ናቸው።

Exit mobile version