አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ 993 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለስ መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱት 993 ኢትጵያውያን 955ቱ ከሳዑዲ የተመለሱ መሆናቸውን ተገልጿል።
መግለጫውን የሰጡት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ 75ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እንደመስራችነቷ ለባለብዙ ወገኖች መድረክ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየችበት ነው ብለዋል።
የድርጅቱን የሪፎርም አጀንዳ የተመለከተው 37ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ላይም ኢትዮጵያ ጥቅሟን በሚያስጠብቅ ሁኔታ የተሳተፈችበት መሆኑን አንስተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተመራ ልዑክም በሱዳን በጎርፍ ለተጎዱ ሱዳናውያን ያደረገው ድጋፍም በሱዳናውያን በኩል መልካም ስሜትን የፈጠረ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል አምባሳደር ዲና።
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጉብኝት አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም በመሪዎች ደረጃ የሚደረግ መሰል ግንኙነት ሀገራቱ በሁለንተናዊ ዘርፍ ለሚያደርጉት መቀራረብ እና ግንኙነት መልካም ውጤት ያመጣል ተብሎ እንደሚታመንበት አስረድተዋል፡፡
በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ዜጎችን በተጠናከረ ሁኔታ ወደ ሀገር የመመለሱ ጉዳይም የማጣራት ሂደቱ ጊዜ መውሰድ ብሎም መዘናጋት በሚፈለገው ልክ እንዳይሆን እንዳደረገው ጠቅሰው ይህንኑ ለማሻሻልም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ረገድም ጀርመን እና ህንድን ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር ተሳትፎና ውይይቶች እንደነበሩም ገልፀዋል።
በሀብታሙ ተክለስላሴ

