Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በትግራይ ክልል የታወጀው የተናጥል የተኩስ አቁም ኢትዮጵያ ለተደቀነባት የውጭ ስጋት መዘጋጀት ስላለባት የተወሰነ ነው – ሌ/ጀ ባጫ ደበሌ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 23 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በትግራይ ክልል የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፎ የወጣው ኢትዮጵያ አሁን ላይ ለተደቀነባት ትልቅ የውጭ ስጋት መዘጋጀት ስላለባት መሆኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ ገለጹ።

ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ዛሬ በጋራ በትግራይ ክልል ስለታወጀው የተኩስ አቁም ስምምነት መግለጫ ሰጥተዋል።

በትግራይ ክልል ጁንታው ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር መደበኛ ጦርነት ማድረግ የቻለው ለሶስት ሳምንታት ብቻ መሆኑንም በዚህ ወቅት ገልጸዋል፡፡

የህውሃት ቡድን ባለፉት ወራት ህዝቡን በዘር በመቀስቀስ ከሰራዊቱ ጋር እንዲጋጭ ሲሰራ ነው የቆየው ብለዋል ።

ህዝቡን ለመማገድ ከመስራት ባለፈም ህውሃት አሁን ላይ ለኢትዮጵያ ትርጉም ያለው ስጋት ሊሆን ከማይችልበት ደረጃ ደርሷልም ነው ያሉት።

አሁን የኢትዮጵያ ስጋት የውጭ ሃገራት ጣልቃ ገብነት በመሆኑ ለዚህ መዘጋጀት አስፈላጊ እና አስገዳጅ በመሆኑ ጦሩ ለቆ እንዲወጣ መወሰኑን አስረድተዋል ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው መንግስት በትግራይ ክልል ያደረገው የተናጥል የተኩስ አቁም እርምጃ ሰብዓዊነት የተላበሰ ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደሆነም ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል አርሶ አደሮች የመኸሩ ጊዜ ሳያልፍ ወደ እርሻ እንዲገቡ ታቅዶ ውሳኔ መሰጠቱንም ነው አምባሳደር ሬድዋን የተናገሩት።

ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ማግለል እና ማዋከብ እየደረሰባት መሆኑንም አንስተዋል።

ይህ አሁናዊ የዲፕሎማሲ ጫና እና በየጊዜው የሚደረጉ የተናጥል እና የጋራ የጦር ልምምዶች ወዴት ሊያመሩ እንደሚችሉ ስለማይታወቅ ሀገራዊ አቅምን አሰባስቦ ለመዘጋጀት ማስገደዱን አስረድተዋል።

በአላዛር ታደለ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version