Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መንግስት በትግራይ ክልል የተናጥል የተኩስ አቁም ማድረጉን ሃገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና እየሰጡት ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የተናጥል የተኩስ አቁም ማድረጉን ሃገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና እየሰጡት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ከዚህ ቀደም ጥያቄ ሲያቀርቡ የነበሩ አካላት እርምጃውን አድንቀዋል ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ስዊዲን፣ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች እርምጃውን እውቅና ከሰጡ ቀዳሚ ሃገራት መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

እርምጃው የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለማክሰም ማገዙንም አውስተዋል፡፡

አያይዘውም በመንግስት ከተጠቀሱ ምክንያቶች ባለፈ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጣቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ውሳኔን ተላልፏልም ነው ያሉት፡፡

አምባሳደር ዲና በሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት የመመለሱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን በማንሳት 9 ሺህ 902 ዜጎች መመለሳቸውን ጠቅሰዋል።

ከእነዚህ መካከል 861 ሴቶች እንዲሁም 193 ደግሞ ህጻናት ተመልሰዋል ብለዋል።
በተጨማሪም ከሃርጌሳ 33 እንዲሁም ከፑንትላንድ 73 ዜጎች መመለሳቸውንም ጠቁመዋል።

በፖለቲካ ዲፕሎማሲ ዘርፍ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በአብዬ ግዛት ያለው ሚናን የተመለከተ ውይይት መካሄዱንም በመግለጫቸው አንስተዋል።

በሱዳን መንግስት በኩል የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ከአብዬ ግዛት እንዲወጣ መጠየቁን ተከትሎ ጦሩ የሰላም ማስከበር ሚናው ጉልህ በመሆኑ ላይ ከመግባባት ላይ መደረሱን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

በዚህ ሳምንት በተካሄደው 72ኛው የኢጋድ ስብሰባ በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ የተካሄዱ ምርጫዎች ሰላማዊ ስለመሆናቸው መገለጹንም አውስተዋል።

ግብጽና ሱዳን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የታላቁ ህዳሴ ግድብን የተመለከተ ላስገቡት ደብዳቤ ኢትዮጵያ ተገቢውን ምላሽ ሰጥታለችም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት የሶስትዮሽ አፍሪካ መር ድርድርን እንዲደግፍ በደብዳቤ መጠየቋንም አስታውሰዋል፡፡

በምስክር ስናፍቅ እና ወንደሰን አረጋኸኝ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version