አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር “ብሄራዊ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት” በኢትዮጵያ ይፋ አደረገ፡፡
ስርዓቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የስራ ፍላጎትና ቅጥር የሚሰንድ፣ ስራ ፈላጊና ቀጣሪን በቀላሉ የሚያገናኝና አጠቃላይ የስራ ገበያን የሚያስተዳድር ዲጂታል ስርዓት ነው ተብሏል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ÷ የስራ ፍላጎትና አቅርቦት የተሳለጠና የዘመነ እንዲሆን ብሄራዊ የስራ ገበያ ስርዓቱ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ያቀድነውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስርአት ወደ ላቀ ደረጃ ከማሸጋገሩ በተጨማሪ ዜጎች በተለይም ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል የሥራ ገበያ መረጃን በተሻለ ፍጥነትና በበቂ መጠን እንዲያገኝ ያስችላልም ብለዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ ÷ሚኒስቴሩ ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር የሚዘረጋው ብሄራዊ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓቱ የተቋማትን መናበብና በጋራ መስራት ስለሚጠይቅ ሁሉም ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ስራውን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የዓለም የስራ ድርጅት እና ጂ አይ ዜድ በትብብር ያከውኑታል ነው የተባለው፡፡
ብሄራዊ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት ግንባታና ትግበራን በጋራ ለመስራት የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የቃል ኪዳን የፊርማ ስነ-ስርዓት ማድረጋቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

