Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የህዳሴው ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በሰኬት እንዲከናወን የመከላከያ ኃይል በአስተማማኝ ዝግጁነት ላይ ይገኛል- ሌ/ጄ አስራት ዴኔሮ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በሰኬት እንዲከናወን በቀጣናው የሚገኘው የመከላከያ ኃይል በአስተማማኝ የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌ/ጄ አስራት ዴኔሮ አረጋገጡ።
ሌ/ጄ አስራት በቀጣናው ተልዕኳቸውን እየተወጡ ከሚገኙ የሠራዊት አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንደተናገሩት ፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በትኩረት የሚከታተለውን የግድቡን ግንባታ በየደረጃው ባሉ አመራርና የሠራዊቱ አባላት ሌት ተቀን አስተማማኝ ጥበቃና ክትትል በማድረግ ግንባታው ያለምንም እንቅፋት በታቀደለት መሠረት እየተፋጠነ ይገኛል።
ሠራዊቱ በከፈለው መስዋዕትነት የመተከል ዞን ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመው ፣ በዞኑ አምስቱ ወረዳዎች ሞትና መፈናቀልን ማስቆም ተችሏል፡፡
ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን በየወረዳቸው የተመረጡ ስፍራዎች የመመለስ ስራ በስኬት ስለመከናወኑም ተናግረዋል።
በቀጣይም የዞኑን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የጀመረውን ተልዕኮ በማጠናከር ግዳጃችሁን በላቀ ብቃት መፈፀም ይጠበቅባችኋል ሲሉም አሳስበዋል።
በመተከል ዞን የመጣው ለውጥ የሠራዊቱ እና የህዝባችን ድምር ውጤት ነው ያሉት ሌ/ጄ አስራት ዴኔሮ ፣ የተገኘውን ድል ለማስቀጠል እና የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በማንኛውም ሰዓት በየትኛውም ቦታ ሠራዊታችን ዝግጁ ነው ማለታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version