አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የመጀመሪያውን የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን በአዲስ አበባ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡
ኮንቬንሽኑ ወደ “እውቀት መር ኢኮኖሚ” በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ይህ ኮንቬንሽን÷ የፈጠራና የምርምር ስራዎችን ለማበረታታት፣ እውቅና ለመስጠትና ትስስር ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ 57 የመንግስትና የግል ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምርና ቴክኖሎጂ ተቋማት፣ 51 የቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ አንጋፋና ወጣት ሳይንቲስቶች፣ የኢንዱስትሪ መሪዎች ፣ ከፍተኛ ባለሃብቶችና ኢንቨስተሮች ተሳተፈዋል፡፡
በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች፣ የባንክና ኢንሹራንስ መሪዎች፣ ታዋቂ ሀገር በቀል እውቀት አቃቢዎችና ፖሊሲ አውጪዎች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘወዴ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በሳይንስና ምርምር በመደገፍ መፍትሄ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
መሰል ኮንቬንሽን ኢትዮጵያ በዘርፉ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ሀብት ማግኘት የሚያስችል፣ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ፣ ሀገር በቀል እውቀቶችን አዘምኖ ለመጠቀም፣ ምርምርና ግኝቶችን ለተቋማትና ለፖሊሲ አውጪዎች ማድረስ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለጥበብ አዲስ አይደለችም ያሉት ፕሬዚዳንቷ÷ ሀገር በቀሉን እውቀት በሳይንስ መደገፍ ትልቅ የቤት ሥራ ስለመሆኑም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሀገሪቱ የአስር ዓመት የልማት መሪ እቅድ ውስጥ የተያዘውን የኢንዱስትሪና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ማኅበራዊ እድገት ለማሳካት አጋዥ እንደሚሆንም አንስተዋል፡፡
ለዚህም ለትምህርት፣ ለኢንዱስትሪ ፣ለቴክኖሎጂና ለምርምር ትስስር መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ነው ያሉት።
የማኅበረሰቡን የሳይንስ ባህል ለማሳደግ ተቋማት ተናበው ሊሰሩ ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ÷ የትምህርት ሥርዓቱን ፈላጊና ተፈላጊን የሚያገናኝ እንዲሆን መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው÷ በቀጣይ አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ የምትተገብረውን የብልፅግና ፍኖተ ካርታ በእውቀት ለመደገፍ ይሰራል ብለዋል።
ጥራት ያላቸው የክህሎት ስልጠናዎችን በበቂ ደረጃ ማረጋገጥ አለብን ያሉት ሚኒስትሩ ÷ የተቋማት ትብብርም ያልዘመነና ያልተሠራበት በመሆኑ መሰል አይነት ዝግጅቶች የጎላ ድርሻ እንደሚኖራቸው አንስተዋል።
ሳይንሳዊና ሀገር በቀል እውቀቶችን አቀናጅቶ ለመጠቀም የሚያስችል ሥርዓት ለመገንባት እንደሚሠራም ነው የገለጹት።
በአፈወረቅ እያዩ
ተጨማሪ መረጃ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር


