Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መንግስት ቀጠናውን ለቆ የወጣው ለህዝቡ እረፍትና ለሰላም እድል ለመስጠት ነው – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ቀጠናውን ለቆ የወጣው ለህዝቡ እረፍትና ለሰላም እድል ለመስጠት እንጂ የግጭት ቀጠና ስፍራ ለመቀየር አለመሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ፡፡

ሚኒስትር ዲኤታው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ መንግስት ተገዶ በገባበት የህግ ማስከበር ዘመቻ የደረሰው ጉዳት ግዙፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም መንግስት ተጨማሪ ኪሳራን፣ የህዝብ ጉዳትን እና እልቂትን ለማስቀረት መሰረቱን ሰብአዊነት ላይ ያደረገ የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የሀገር ሉአላዊነት ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን ግምት ውስጥ ያስገባና ተያያዥነት ያላቸውን ምክንያቶች ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ሰራዊቱ የግጭት ቀጠናውን ለቆ ሲወጣ “አታጅቡን አትከተሉን እኛው በተመቸን መንገድ ብቻችንን ተንቀሳቅሰን እርዳታ ማድረስ አለብን” ሲሉ ለነበሩ አካላት እድል እንደሰጠም አቶ ሬድዋን በመግለጫቸው አብራርተዋል፡፡

የመንግስት ውሳኔ ፍተሻ የሚደረግባቸው ኬላዎች ይነሱልን፣ በፍተሻ የሚስተጓጎል ሰዓት አይኑር እና ነፃ አድርጋችሁ ልቀቁን በሚል ግፊት ሲያካሂዱ ለነበሩ አካላትም መልስ የሰጠ ነበርም ብለዋል፡፡

ግጭቱን ጋብ በማድረግ የተኩስ አቁም ወስኑና ዕርዳታ በቀላሉ ማድረስ የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠር አርሶ አደሩም ይረስ ሲሉ ለነበሩ አካላትም ምላሽ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

“የአዝመራው ጊዜ ካለፈ ረሀብን እንደመሳሪያ ተጠቅማችኋል ብለን እንከሳችኋለንና አዝመራው ሳያልፍ እና የእርሻው ጊዜ ሳይስተጓጎል ተኩስ አቁማችሁ አርሶ አደሩ ማረስ የሚችልበት ዕድል መፈጠር አለበት የሚል ውትወታ ሲያካሂዱ ለነበሩም ውሳኔው ይጠቅማል ነው ያሉት፡፡

አሸባሪው ህወሓት የተናጠል የተኩስ አቁሙን ወደ ጎን በመተው አፍራሽ ተግባር ፈጽሟል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፥ የእርዳታ ድርጅቶችም መንግስት በስፍራው በነበረበት ወቅት ሲያቀርቧቸው የነበሩ ተገቢነት የሌላቸው ክሶች አሁንም መቀጠላቸውን አውስተዋል፡፡

የውጭ ሀገራትም ሆኑ በእርዳታ ስም ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡትን መንግስት አይታገስምም ነው ያሉት፡፡

በእርዳታ ስም የሽብር ቡድኑን መሳሪያ ለማስታጠቅ የሚደረጉ ሙከራዎች መኖራቸውን እና መንግስት በሰጠው የጥሞና ጊዜ ለውጥ ከሌለ ሀገር ለማዳን ሲል መንግስት ውሳኔውን ዳግም እንደሚፈትሽም ነው የተናገሩት፡፡

አምባሳደር ሬድዋን በመግለጫቸው ህወሓት በዓለም የጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቀውን ህፃናትን ለውትድርና የማስገደድ ተግባር ዓለም አቀፍ ተቋማት በአወንታ ማየታቸው ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ከዚህ አንጻርም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን ተግባር በፅኑ እንዲያወግዝም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version