Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሁሉም ዜጋ የሀገር ህልውና እና ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ በጋራ ሊቆም ይገባል-የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5 ፣2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁሉም ዜጋ የሀገር ህልውና እና ሰላምን ለማስጠበቅ በጋራ ሊቆም ይገባል” ሲሉ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።

ኢትዮጵያ ከገጠሟት ፈተናዎች በድል ትወጣ ዘንድ የሃይምኖት አባቶች ሀገራቸውን በጸሎት እንዲያስቡም ተጠይቋል።

“እኛ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን ትተን በጋራ የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው” ያሉት አባቶቹ፤ የሀገር ህልውናን ማስጠበቅ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ሃላፊነት እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የመከላከያ ሚኒስትርና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በጋራ በመሆን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ተወያይተዋል።

በመድረኩም አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያከናወናቸውና እያከናወናቸው ያሉ ሴራዎችን በሚመለከት ለሃይማኖት አባቶች ገለጻ ተደርጓል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞጢዎስ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሃት ባለፉት ሶስት ዓመታት በተደጋጋሚ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራውን ቀጥሎበታል።

በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶችን እንዲነሱ በፋይናንስ ጭምር በመደገፍ ምንም የማያውቁ አርሶ አደሮች ህይወት እንዲጠፋና ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉንም ነው ያስታወሱት።

የሃይማኖት አባቶች ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ወደ መቀሌ በተደጋጋሚ በመመላለስ አባታዊ ኃላፊነታቸውን እንደተወጡ ያስታወሱት ዶክተር ጌዲዮን፤ የሽብር ቡድኑ ግን በአጉል ትዕቢት የሰላም አማራጮችን በሙሉ ወደ ጎን መግፋቱንም ተናግረዋል።

ሰላም በአንድ ወገን ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑ መንግስት ተገዶ ወደ ጦርነት መግባቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ፤ የሽብር ቡድኑ በአሁኑ ወቅት በትግራይ አጎራባች ክልሎች ወረራ በመፈጸም አጅግ አሰቃቂ ወንጀል እየፈጸመ መሆኑን አብራርተዋል።

“በዚህም መንግስት ለትግራይ ህዝብ አስቦ ያወጀውን የተናጥል ተኩስ አቁም መልሶ እንዲያነሳው ተገዷል” ብለዋል።

በመሆኑም የሃይማኖት አባቶች የሽብር ቡድኑ ህጻናትን ጨምሮ ንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ ተገንዝበው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በበኩላቸው፤ አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት በእነርሱ ቢደርስ የማይታገሱትን ጥፋት ኢትዮጵያ እንድትሸከመው የሚያደርግ ፍርደ-ገምድል አካሄድ እየተከተሉ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደተደረገበት የገለጹት ኮሎኔል ጌትነት፤ “ሠራዊቱ ለኢትዮጵያውያን ቀርቶ ለየትኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ክብር እንዳለው በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አስመስክሯል” ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች ምዕመናን በማስተማር የሀገር ህልውና እንዲጠበቅ ሃላፊነታቸውን ከመወጣት ባለፈ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግን የውጭ ጣልቃ ገብነትን እንዲያወግዙ ጠይቀዋል።

የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው ችግሩ በመሰላም እንዲፈታ በተደጋጋሚ ሲጥሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ የሽብር ቡድኑ ይህን ጥረት ወደ ጎን በመግፋቱ የማይፈለግ ዋጋ መከፈሉን አንስተዋል።

የሃይማኖት አባቶች ዜጎች አንድነታቸውን ጠብቀው ለሀገር ህልውናና ሰላም ዘብ እንዲቆሙ ማስተማር እንዳለባቸውም አንስተዋል።

“እኛ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን በመተው በጋራ የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው” በማለት ሃይማኖት አባቶች ገልጸዋል።

የሀገር ህልውናን ማስጠበቅ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ሃላፊነት እንዳልሆነም አስገንዝበው፤ የእምነት ተቋማት ለሀገር ህልውናና ሰላም ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

መንግስት ትክክለኛ መረጃዎችን በፍጥነት ለህዝብ በማድረስ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሆን ተብሎ የሚፈጠርን ውዥንብር መከላከል እንዳለበትም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሃይማኖት ካባ በመልበስ ህዝብን የሚያደናግሩ ግለሰቦች ላይም ቁጥጥር እንዲደረግ ጠይቀዋል።

Exit mobile version