አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 7፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የኦሮሚያ ክልል መንግስት አሸባሪው ጁንታ ቡድን በአፋር ህዝብ ላይ በከፈተው ጦርነት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የምግብና የመድኃኒት ድጋፍ አደረገ፡፡
ድጋፉን በአፋር ሰመራ ተገኝተው ለአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ያስረከቡት የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አማካሪ አቶ ግርማ ዋፈሬ ናቸው፡፡
በዚህም 2ሺህ ኩንታል እህል ፣ 1 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የህክምና መድሀኒቶች የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ድጋፍ ማድረጉን በርክክቡ ስነስርዓት ወቅት ተገልጿል።
ከ7 ሚሊየን 500 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መሆኑን የተናገሩት አቶ ግርማ÷ለአፋር ክልል ተጎጂዎች ይህ የድጋፉ ማሳያ እንጂ በቂ አይደለም ተጠናክሮም ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
ክልሉ ከአፋር ህዝቦች እና ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን ሽብርተኛው ቡድን ፈጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ በጋራ ይሰራል ብለዋል፡፡
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው÷ ስለተደረገው ድጋፍ አመስግነው በአሁኑ ሰዓት የጁንታው ሀይል እየተደመሰሰ ይገኛል ብለዋል፡፡
ቡድኑ በትግራይ ህዝብ ደም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየሰራ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ በአፋር በኩል የሽብርተኛው ሀይል ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰበት ገልፀዋል፡፡
የአፋርን ህዝብ ለማጥፋት ሉዓላዊነቱን ለመዳፈር የሞከረውን ሀይል በመደምሰስ የኢትዮጵያን አንድነት አስከብረን እንቀጥላለን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አትዮጵያ የጋራ ቤታች ናት፤ የጁንታው የጋራ ቤታችንን የማፍረስ ሴራም ቅዠት ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአወል አበራ እና ጥበበስላሴ ጀንበሩ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

