አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ካለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ሁኔታውን የሚያዩበት መንገድ መለያየትን የሚያባብስና ሃላፊነት የጎደለው ሆኖ መታየቱን ሩሲያ አስታወቀች።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ እየተካሄደ ያለውን የህልውና ዘመቻና ወቅታዊ ጉዳዮች በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባይዋ በመግለጫቸው አሸባሪው ህወሓት አሁንም ድረስ ወደ ውጊያ በመግባት ወደ አፋር እና አማራ አጎራባች ክልሎች ጥቃት በመሰንዘር የሰብአዊ ድጋፍ እንዲስተጓጎል ማድረጉንና የኢትዮ-ጂቡቲን መስመር ለመዝጋት ጥቃት መፈጸሙን ገልጸዋል።
“ቡድኑ ከክልሉ በማለፍ ያደረሰው ጭፍጨፋና ጥቃት ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈለጋቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ድጋፍ እንዳያገኙ አድርጓል” ብለዋል።
“ለእነዚህ ችግሮች መከሰት የአንዳንድ የምዕራባውያን የሚዲያ አካላት ሚናም ከፍተኛ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል” ነው ያሉት።
የእነዚህ አካላት እንቅስቃሴ ሰላምን ከማምጣት ይልቅ ሀላፊነት በጎደለው ተግባር ጥፋትን ማባባስና ልዩነቶችን የማቀጣጠል ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
“ደም መፋሰሱን ለማስቆም፣ የሰብአዊ ሁኔታን ለማሻሻል፣ ማህበረ-ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠርና ተፈናቃዮችን ወደ ቋሚ መኖሪያቸው ለመመለስ በሁለቱም በኩል የተኩስ አቁም ማወጅ ብቸኛው አስተዋይ መንገድ ነው ብለን እናምናለን” ብለዋል ቃል አቀባይዋ።
“በትግራይ ክልል ሰላምን ለማምጣትና ወደ መደበኛ የህይወት እንቅስቃሴ ለመመለስ በኢትዮጵያ መንግስት እየተከናወነ ያለውን ተግባር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ቀጠናዊ ተቋማትን እንዲደግፉ ጥሪ እናቀርባለን ሲሉም አስታውቀዋል።
“ሩሲያ ኢትዮጵያውያን የውስጥ ጉዳያቸውን ከአፍሪካውያን ጋር በራሳቸው ለመፍታት ወሳኝ ሚና መጫወት አለባቸው ብለን እናምናለን” ሲሉ መግለጻቸውን በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ አስታውቋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

