አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የእርዳታ ስራ የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥል መንገድ መከወን እንዳለበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ መሠረት አድርገው የሀገሪቱን አሰራር ተከትለው ድጋፍ እያደረጉ ላሉ የእርዳታ ድርጅቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ምስጋና ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡
የእርዳታ ድርጅቶቹም ከእርዳታ ፍሰት እና ከፍተሻ እና ከባንክ አገልግሎት፣ ከቪዛ እና ከኮሙዩኒኬሽን መሣሪያዎች ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች ማቅረባቸውንም አንስተዋል።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች አሸባሪው ህወሓት ትንኮሳውን መቀጠሉ ለእርዳታ አቅርቦት ስራዎች እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል ማለታቸውንም ቃል አቀባዩ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በኩል የፍተሻ ጣቢያዎችን ቁጥር ለመቀነስና ዘመናዊ በማድረግ አገልግሎቱን ለማፋጠን እንደሚሰራ ለዓለም ዓቀፍ ድርጅቶቹ ተገልፆላቸዋል ተብሏል፡፡
የእርዳታ ስራዎች የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥል መንገድ መሆን እንዳለበትም አውስተዋል፡፡
መንግስት ሁሉን አቀፍ ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑም በመግለጫው ተነስቷል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል እርዳታን በተመለከተ የሚናፈሱ አሉታዊ ትርክቶች መኖራቸውን እና በዚህ በኩል እርምት እንዲወሰድም ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ከሕዳሴው ግድ ጋር በተያያዘ ሁሉም የላይኛው የተፋሰሱ ሃገራት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን እንዲፈርሙ ኢትዮጵያ ጠይቃለች ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ከሳዑዲ አረቢያ 1 ሺህ፣ ከየመን 1 ሺህ 200 ዜጎች እንደሚመለሱም አንስቷል፡፡
ባለፈው ሳምንትም ከሳዑዲ 1 ሸህ 665 ዜጎች የተመለሱ ሲሆን÷ በተመሳሳይ ከየመን 1ሺህ 200 ዜጎችን ለመመለስ የሚያስችል የጉዞ ሰነድ ዝግጅት ተጠናቋል ተብሏል፡፡
በወንደሰን አረጋኸኝ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

