Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሚሊየኖች የተሳተፉበት የሆራ አርሰዴ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መሰከረም 23፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሚሊየኖች የተሳተፉበት የሆራ አርሰዴ በዓል በተረጋጋ ሁኔታና ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቀረቡ፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ በዓሉ በሰላም መጠናቀቁን ምክንያት በማድረግ በሰጡት መግለጫ÷ የኢሬቻ ማክበሪያ ቦታ የእርቅ፣ የፍቅር እና የይቅርታ ቦታ እንጂ የጥላቻና የፖለቲካ መድረክ እንዳልሆነ የኦሮሞ ህዝብ በአንድነት አስመስክሯል ብለዋል፡፡

የበዓሉን እሴቶች ለማደናቀፍ የታቀዱ እኩይ ሙከራ ከሽፏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉ እሴትና ክብር ጠብቆም ተከናውኗል ብለዋል፡፡
በዚህም በዛሬው እለት የታየው ጨዋነት ደግሞ የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል አቶ ሽመልስ፡፡

ኢሬቻ የዳበረ እና በአኩሪ እሴት የተሞላና ወደ ቀደመ ባህል ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥን ነው ሲሉም በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡

ኢሬቻ የሚከናወንበት መልካ÷ አንድነት የሚጠነክርበት፣ የብሄር ብሄረሰቦች ወንድማማችነት የሚወደስበት፣ ተስፋና ምኞት የሚመሰከርበት እንጂ የፍራቻ እና ስጋት ምንጭ እንዳልሆነ ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ እና ኢሬቻ ሆራ አርሰዴ ህያው ምስክር ናቸው ብለዋል፡፡

ይህ እሴት ከየትኛውም ንክኪ ነፃ መሆን አለበት ብለዋል፤የኦሮሞ ህዝብ ኢሬቻን ከጫና እና ከንክኪ ጠብቆ ለአሁኑ ትውልድ እንዳስረከበ ሁሉ ይህ ትውልድም ተንከባክቦ ለሚቀጥለው እንደሚያስተላልፍ ጥርጥር የለኝም ብለዋል፡፡

ሆራ አርሰዴ የኢሬቻ በዓል እንደ ሆራ ፊንፊኔው ሁሉ በአማረ እና ህዝቡን በሚመጥን መልኩ እንዲከበር የአባገዳዎችና ሃደሲንቄዎች ድርሻ ከፍተኛ ነው፤ በበዓሉ ህዝቡ የገዳ አባቶች ያስተላለፉትን መልዕክት ተግባራዊ በማድረግ የመደማመጥና የመታዘዝ ባህልም ከፍ ያለ መሆኑ ታይቷል፡፡

ቄሮ፣ ቀሬና ፎሌ በመተባበር በዓሉ በሰላም እንዲከበር ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበው ፤የጸጥታ አካላት በከፍተኛ ሃላፊነት ስሜት የህዝባችንን ደህንነት በመጠበቅ የህዝብ አለኝታ መሆናቸውን በድጋሚ አስመስክረዋል ብለዋል፡፡

በዚህም ህዝባችን በእናንተ ይኮራል ያለ አንዳች ስጋትም ገብቶ ይወጣል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ÷የመንግስት ሃላፊዎችና ሚዲያዎች ለበዓሉ ስኬት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለመንግስት ምስረታ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version