Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነት እና ጽናት ውጤት ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነት እና ጽናት ውጤት ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ መመረቁን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ትችላለች” በሚል መሪ ሃሳብ የሕዳሴ ግድብን የ14 ዓመት ጉዞ የሚያስቃኝ የፎቶ እና ስዕል ዓውደ ርዕይ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከፍቷል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሁነቶችን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነት፣ አይበገሬት እና ጽናት ውጤት ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በቅንጅትና ትብብር ከሰሩ መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብን የ14 ዓመት ጉዞ በተለይም የሕዝቡን ተሳትፎ የሚያሳይ የፎቶ፣ የስዕል እና በዓባይ ዙሪያ የተጻፉ መጽሐፍት ዓውደ ርዕይ እና የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ መካሄዱን ጠቅሰዋል፡፡

በፖናል ውይይቱ የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ፣ ከጂኦስትራቴጂካዊ ኩስምና ወደ ታደሰ ቁመና መሸጋገር፣ የሕዝብ አንድነትና ተሳትፎ ትርጉም አስመልክቶ በምሁራን ትንታኔ መቅረቡን የከተማዋ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባለፉት 14 ዓመታት ያለፈበት ውጣ ውረድ፣ የተገኙ ድሎች፣ የውሃ ፖለቲካ ምንነት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ጽሑፎች ቀርበው ወይይት መካሄዱም ተመላክቷል፡፡

በመርሐ ግብሮቹ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ እና በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ተገኝተዋል።

እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራልና የከተማ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

Exit mobile version