Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የማርበርግ ቫይረስን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር በቅንጅት እየተሰራ ነው – ዶ/ር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማርበርግ ቫይረስን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው አሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፡፡

ሚኒስትሯ በሰጡት መግለጫ ÷ የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ታማሚ ከተረጋገጠበት ቀን ጀምሮ እስካሁን በበሽታው ለተጠረጠሩ 17 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጓል፡፡

ከዚህ ውስጥም 3ቱ የማርበርግ ቫይረስ እንደተገኘባቸው እና ሕይወታቸው እንዳለፈ መረጋገጡን ነው የገለጹት፡፡

እስካሁን 6 ሰዎች የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ምልክቶች አሳይተው ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን÷ የሽታውን ምልክቶች ካሳዩ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው 129 ሰዎች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል።

ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠርም ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች እንዲሁም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ መሰረትም ድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና ክስተት ፈጣን ምላሽ ዕቅድ በማውጣት በየደረጃው በተቋቋሙ የድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከላት አማካኝነት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን ወደ ቦታው በመላክ የማርበርግ በሽታ ቅኝትና ምላሽ ስራዎች በተቀናጀና በተጠናከረ መልኩ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

እንደሀገር በሽታውን ለመመርመር የሚያስችል የላቦራቶሪ አቅም በመገንባት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ውስጥ በራስ አቅም ምርመራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የተደራጀ የለይቶ ማቆያ እና ማከሚያ ማዕከላት የተቋቋመ ሲሆን÷ በሌሎች ክልሎች ደግሞ በሽታው ቢከሰት ለማከም የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

ለእነዚህም ተቋማት የሚያስፈልጉ የሕክምና ግብአቶችና የኢንፌክሽን መከላከያ ቁሳቁሶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ዶ/ር መቅደስ የበሽታውን ምልክቶች የሚያሳይ ማንኛውም ሰው በወቅቱ ወደ ሕክምና ተቋማት መሄድ የላቦራቶሪ ምርመራ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የበሽታው ምልክቶች ከፍተኛ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለትና ራስ ምታት፣ የጡንቻ እና የጀርባ ህመም፣ ማቅለሽለሽ፣ የሆድ ሕመም እና ተቅማጥ፣ ደረት፣ ጀርባ እና ሆድ ላይ በጣም ጎልቶ የሚታይ ሽፍታ እንዲሁም ከአፍ፣ ከአፍንጫ ወይም ከቆዳ ስር ደም መፍሰስ ናቸው፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version