Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኮንፈረንሱ የኢትዮጵያ እና ቻይናን የትብብር መንፈስ የሚያንጸባርቅ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በቻይና እየተካሄደ የሚገኘው የቻይና-ኢትዮጵያ የቡና ኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ኮንፈረንስ የሁለቱን ሀገራት የትብብር መንፈስ የሚያንጸባርቅ ነው አሉ፡፡

ፕሬዚዳንቱ በቻይና ሁናን ግዛት ጁጆ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ቡና የማስተዋወቅ ኮንፈረንስ አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ኮንፍረንሱ ስለ ቡና ከመነጋገር ባሻገር የሁለቱን ሀገራት የረዥም ጊዜ አጋርነት የሚዘክርና ያላቸውን የትብብር መንፈስ የሚያንጸባርቅ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ የቡና ዝርያዎች መገኛና በስፋት የሚመርትባት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ የቡና ታሪካዊ ቦታ መሆኗን ለዓለም ያሳየችበት ኮንፈረንስ ነው ብለዋል፡፡

ቡና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለአብነትም 30 በመቶ የሚሆነው የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚገኘው ከቡና መሆኑን አንስተዋል፡፡

በቻይና አፍሪካ የትብብር ማዕቀፍ መሰረት ኢትዮጵያ እና ቻይና ለኢንዱስትሪ ሽግግር ወሳኝ በሆኑት ግብርና፣ የገጠር አረንጓዴ ልማት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና መሰረተ ልማት ዘርፎች የጋራ ርዕይ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ረገድ ለኢትዮጵያ የቡና ምርት የገበያ እድሎችን ለማስፋት የሚያስችሉ መሰል መድረኮች ወሳኝ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸው፥ ይህንን ኮንፍረንስ ያዘጋጁ አካላትን አመስግነዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version