Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዛሬው ዕለት ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊነትና ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ አንድ እጥፋት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ መጀመር ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊነትና ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ አንድ እጥፋት ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ይፋዊ በሆነ መርሐ ግብር ዛሬ በስፍራው አስጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ዕለቱ ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊነት እና ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ አንድ እጥፋት ነው፡፡

ኢትዮጵያ እምቅ አቅሟን እና ታላቅ ርዕይዋን የሚመጥን ሌላ ተጨማሪ ሜጋ ፕሮጀክት ጀምራለች ነው ያሉት።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ይሆናልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር የኩራት ምንጭ መሆኑንና ይህ የሆነውም ያለተግዳሮት በመጓዙ ሳይሆን በጽናት በተሞላው እንቅፋቶችን የመሻገር አቅሙ እና በአፍሪካ የፋና ወጊነት ሚናው የተነሳ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአየር መንገዱ ትልቁ ጥንካሬ የሚመነጨው ከጠንካራው ተቋማዊ ባሕሉ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለጥንቃቄ እና ደኅንነት ቅድሚያ መሥጠት፣ በፈጠራ እና ጠንካራ ሥራ የሚመራ አመራር፣ ከ26 ሺህ በላይ ቁጥር ያለው በአየር መንገዱ ሰንደቅ ተሸካሚነት እና የሚወክለውን በሚያምኑ እና በሚያከብሩ ሠራተኞች እንዲሁም ባላሰለሰ የመማር እና የአቅም ግንባታ ጥረት ላይ የተገነባ አየር መንገድ መሆኑን አብራርተዋል።

ከአዲስ አበባ ደቡብ ምዕራብ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት በ1 ሺህ 910 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ቢሾፍቱ ለአውሮፕላኖች የተመቸ ከባቢ ብሎም ኢትዮጵያን መዳረሻ ለሚያደርጉም ሆነ ለትራንዚት መንገደኞች ምቹ አቀባበል የተመቸች ያደርጋታል ነው ያሉት።

ፕሮጀክቱ ብዛት ያላቸው የተሽከርካሪ መስመሮችን የያዘ አዲስ አበባን ከአዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ የሚያገናኝ ዘመናዊ መንገድ ግንባታን ያካተተ ሲሆን÷ በሰዓት ከ120 እስከ 200 ኪሎ ሜትሮች ፍጥነት ያለው የከፍተኛ ፍጥነት የባቡር ሀዲድ እና ሥርዓት ግንባታን አካትቷል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመጀመሪያው ምዕራፍ በዓመት 60 ሚሊየን መንገደኞችን ለማስተናገድ የሚችል ሲሆን÷ በታቀደው መሠረት ሙሉ ግንባታው በሚጠናቀቅበት ወቅት በዓመት እስከ 110 ሚሊየን መንገደኞችን ያስተናግዳል።

ይህም ኢትዮጵያን ከዓለም ግንባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት ማዕከላት አንዷ እንደሚያደርጋት መገለጹን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version