አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል አዲሱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ሀገርን የሚመጥን የፖሊስ አገልግሎት መስጠት ያስችላል አሉ።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለውጥ መደረጉ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በመከላከል እና በመቆጣጠር የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
ነባሩ የፌዴራል ፖሊስ ተሽከርካሪ ሰሌዳ ከ50 ዓመታት በላይ የቆየ፣ የተዘበራረቀና ወጥነት የጎደለው እንደነበር አስታውሰው÷ ይህም ለቁጥጥር አመቺ እንዳይሆን ማድረጉን አብራርተዋል፡፡
ፖሊስ ሀገርና ዘመኑን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ ÷ አዲሱ የፖሊስ ሰሌዳ በስራ ላይ መዋሉ የወንጀል ምርመራና ክትትል ስራን ማዘመንና ማሳለጥ እንደሚያስችል አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አዲሱ የተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ከቴክኖሎጂ እና ከመረጃ ቋት ጋር የተጣመረ መሆኑን ገልጸው÷ መሰል አገልግሎቶችን ከቴክኖሎጂ ጋር የማስተሳሰር ስራዎች የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ጉዞ ማሳያ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ በርኦ ሀሰን በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለውጥ ዘመኑን የዋጀና ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂ የሰጠችውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር አጠቃላይ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለውጥ ሥራን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ነው ያመላከቱት፡፡
በጀማል አህመድ

