አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ የምዘና ስርዓት ለመገንባት ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የፈተና ብሔራዊ ግብረ ኃይልን የቅደመ ዝግጅት ስራዎችና የደረሰበትን ደረጃ ገምግመናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የዲጂታል ፈተና ምዘና ስርዓትና የቅድመ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶችን ግንባታ በተመለከተ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎችን ጨምሮ ከትምህርት ዘርፍ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ሙሉ በሙሉ ወደ ኦንላይን ትግበራ ለማሸጋገርና ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ የምዘና ስርዓት ለመገንባት ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበይነ መረብ በተደረገው ውይይት ላይ እንዳሉት፥ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ከተቀመጡ ግቦች አንዱ ደህንነቱ የተጠበቀና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የትምህርትና ምዘና ስርዓት መዘርጋት ነው፡፡
ይህም ተደራሽ፣ ፍትሀዊና ቀልጣፋ የፈተናና ምዘና ስርዓት በማስረፅ ተማሪዎቻችን መጪውን ዘመን የዋጁ እንዲሆኑ ለማድረግ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
በሁሉም ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች በተመሳሳይ የጥራት ደረጃ 1ሺህ 452 ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ መጪው ነሀሴ ወር ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች እንዲሁም ከቅድመ አንደኛ እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ የሚያገለግሉ መጽሀፍት እስከ መጪው መስከረም ወር ድረስ ታትመው ወደ ትምህርት ቤቶች እንዲሰራጩ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን አመልክተዋል፡፡

