Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሰራዊቱን የውጊያ ዝግጁነትና የጤና ተደራሽነት ለማሳደግ የሚያስችል ሪፎርም ተደርጓል – አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰራዊቱን የውጊያ ዝግጁነት ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ የጤና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ተደርጓል አሉ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)፡፡

መከላከያ ሚኒስቴር ፓዲያት የጤና አገልግሎት ግሩፕ ከተሰኘ የሕንድ ዓለምአቀፍ ኩባንያ ጋር የጤና ኢንዱስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር የትብብር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ስምምነቱ የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታልና ዲያግኖስቲክ ግሩፕ የሚሰጠውን አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው፡፡

የትብብር ስምምነቱ ሆስፒታሉ በጤና ግሩፕነት እንዲዋቀር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ገቢራዊ ማድረግ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም የተቋሙን የህክምና መሰረተ ልማት፣ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር በማሳደግ የላቀ የጤና አገልግሎት በኢትዮጵያ ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የሰራዊቱን የውጊያ ዝግጁነት ለማረጋገጥና የጤና ተደራሽነቱን ለማሳደግ ከግንባር መስመር እስከ ሪፈራል ሆስፒታል የጤና መሰረተ ልማት በመገንባት በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ሪፎርም መደረጉን ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፥ የሁለቱ ተቋማት ስምምነት መንግስት ለሕዝቡ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የገባውን ቃል ተግባራዊ ያደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።

መከላከልና አክሞ ማዳንን መሰረት ባደረገ የጤና ፖሊሲ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ስምምነቱ ከሀገር ባለፈ የአፍሪካን የጤና ቱሪዝምን ማጠናከር ያስችላል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩመር ራይ በዚሁ ወቅት፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ትብብር እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

Exit mobile version