አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ኢትዮጵያ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ስኬታማ የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ማሻሻያ አድርጋለች አሉ።
የኢትዮ-እንግሊዝ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም 2026 በለንደን የተካሄደ ሲሆን÷ በጎንዮሽም በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂና ዲጂታላይዜሽን ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
ቢልለኔ ስዩም በዚህ ወቅት ፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የዲጂታላይዜሽን ሒደት ዋና ስትራቴጂዎችን ወደ ላቀ ምዕራፍ እያሸጋገረ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የዲጂታል ዘርፍ እመርታ፣ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሁም ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለማዕድንና ለቱሪዝም ዘርፎች መሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
አምስቱ የኢትዮጵያ ብዝኅ ኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶዎች በዲጂታል መሠረተ ልማት ታግዘው ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ መሆኑንና የዲጂታል ዘርፉ በኢኮኖሚ ሥርዓቱ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ አምጥቷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የበለፀጉ ሀገራት ያለፉበትን ልምድና ተሞክሮ በመውሰድና ከነባራዊ አውድ ጋር በማጣጣም በወሳኝ የሽግግር ሒደት ላይ እያለፈች መሆኗን አብራርተዋል።

