Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካን የጤና ስርዓት ለማጠናከር በመደመር እሳቤ የተመራ አህጉራዊ ትብብር ወሳኝ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአፍሪካን የጤና ስርዓት ለማጠናከር በመደመር እሳቤ አህጉራዊ አቅምንና ጥረቶችን ማስተባበር ይገባል አሉ፡፡

5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ “የአፍሪካ የጤና ደህንነት እና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ የጋራ መግባባት ላይ ሊደረስባቸው የሚገቡ ሦስት የቅድሚያ ጉዳዮችን አቅርበዋል፡፡

በርካታ ዜጎቻችን ልዩ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት አሁንም ረጅም ርቀት ይጓዛሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመሆኑም የመጀመሪያው ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የሕክምና ልህቀት ማዕከላትን ማልማት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ በአፍሪካ ለሚመረቱ ጥራት ያላቸው መድኃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች አስተማማኝ የገበያ ፍላጎት ለመፍጠር የአህጉሪቱን የመግዛት አቅም ማሰባሰብ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ይህም የሀገር ውስጥ አምራቾች በስፋት ኢንቨስት እንዲያደርጉ፣ የምርት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ሌላኛው የቅድሚያ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዕቅዶቻችንን ወደ ተግባር ስንለውጥ ጥብቅ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አለብን ነው ያሉት።

ለእያንዳንዱ ቃል ኪዳን ግልጽ ኃላፊነት የሚወስድ አካል፣ የተረጋገጠ በጀት እንዲሁም የእድገት ደረጃን ለመገምገም የተቀመጠ የጊዜ ሰሌዳ ሊኖር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ስኬታችን የሚለካው ዜጎቻችን በዕለት ተዕለት ህይወታቸው በሚያገኙት የጤና አገልግሎት ላይ በሚታይ ተጨባጭ መሻሻል መሆን አለበት ብለዋል።

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version