አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የመድኃኒት ምርቶችን ጥራትና ደህንነታቸውን ባረጋገጠ መልኩ በሀገር ውስጥ በብዛት ለማምረት እየሠራች ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ “የአፍሪካ የጤና ደህንነት እና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ማዕቀፍ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በመታገዝ የጤና አገልግሎትንና የሀገር ውስጥ መድኃኒት ምርትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ በመድኃኒትና ከውጭ በሚገቡ ክትባቶች የዓለም ጤና ድርጅትን 3ኛ ደረጃ የብቃት ማረጋገጨ ማግኘቷን አስታውሰው፤ ይህም የሀገር ውስጥ የመድሃኒት አምራቾች ለቀጣናው ጭምር እንዲያቀርቡ ጠንካራ መሠረት የጣለ ነው።
ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ከስፔሻሊስቶች ጋር እንዲገናኙና የታካሚዎች መረጃ በየትኛውም የጤና ተቋም ተደራሽ እንዲሆን ቴክኖሎጂ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአህጉሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ዲጂታል የጤና መሳሪያዎች በአፍሪካ ተመራማሪዎች ሊመረቱ እንደሚገባ ገልጸው፤ ለዚህም የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ቀጣይነት ያለው በጀትና በራሳችን ሕግ የሚመራ የጤና መረጃ ጥበቃ ሥርዓት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

