የሀገር በቀል እሴቶች ዘርፈ-ብዙ አስተዋጽኦ…

ሀገር በቀል እሴቶች፣ ለዘመናት በሕዝቦች ዘንድ ተከብረው የቆዩ፣ የሞራል ልዕልና ያላቸው እና ቂም አልባ ዘላቂ ሰላምን ማውረድ የሚችሉ ፍፁም ፈዋሽ የውይይት መድረኮች ናቸው።
ሀገር በቀል እሴቶቻችን የተለያዩ የፖለቲካና የማኅበረሰብ ክፍሎች ጽንፍ የረገጡ ሐሳቦቻቸውን ይዘው ወደ መካከለኛ የውይይት መስመር እንዲመጡና የጋራ ሀገራዊ መግባቢያ ነጥቦችን እንዲቀርጹ ትልቅ ምሳሌ ይሆናሉ።
ሀገር በቀል እሴቶች ለአንድ አካባቢ ብቻ የተወሰኑ ሳይሆኑ፣ መላዋ ኢትዮጵያ ልትማርባቸውና ልትጠቀምባቸው የሚገቡ ብሔራዊ ሀብቶች ናቸው።
ኢትዮጵያ ካጋጠሟት ውስብስብ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቅራኔዎች ወጥታ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በታሪኳ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ሀገራዊ ምክክር እያካሄደች ትገኛለች።
ለዚህ ታሪካዊ መድረክ ስኬታማነት የምዕራባውያን የድርድር ፍልስፍናዎች እንዳሉ ሆነው፣ ሀገር በቀል እሴቶቻችንም ድርሻቸው ከፍተኛ ነው፡፡
ለዚህም ነው እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ ምክክር ውስጥም እንኳን እሴቶቹን የመጠቀም ሥራ የተሰራው፡፡
እነዚህን ሀገር በቀል እውቀቶች በምክክር ሂደቱ ማካተት ፋይዳው የጎላ ነው፡፡
ይህም የምክክሩ ሂደት ስር የሰደደ፣ በባህላችን የተደገፈ እና በሕዝቡ ዘንድ ሙሉ አመኔታና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ያደርገዋል።
ማኅበራዊ ቀውሶችን ለመፍታት፣ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር እና በሕዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማውረድ ፍፁም ፈዋሽ መሣሪያ ናቸው፡፡
የሀገራዊ ምክክር ዋነኛ ግብም የሀገሪቱን የቆዩ ቁስሎች ማከም ነው።
ይህ ቂም አልባ የእርቅ ዘዴ ኢትዮጵያ ካለፉ የፖለቲካ ቁርሾዎች ወጥታ፣ እርስ በእርስ የመወነጃጀል አባዜን አቁማ የጋራ የወደፊት እጣ ፈንታዋ ላይ እንድታተኩር ያደርጋል፡፡
የመደበኛ የፍርድ ቤት ሕግ፣ ጥፋተኛውን በመቅጣት እንዲታረም ያደርጋል፡፡
በበዳይና በተበዳይ መካከል ያለውን የጥላቻ ስሜት ግን ሙሉ በሙሉ ላያጠፋ ይችላል፡፡
የሀገር በቀል እሴቶችና የምክክሩ ሂደት ዋና ዓላማ ፍርደኛን መፈለግ ሳይሆን፣ የተበላሸውን ግንኙነት ጠግኖ ኢትዮጵያን ወደ መግባባትና ሰላም መመለስ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶች ለሀገራዊ መግባባት ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞችን ያበረክታሉ፡፡
እንደ ሽምግልና፣ አበጋር፣ ዱቡሻ፣ ሲንቄ፣ ጉማ፣ ጃካ፣ ሉዋ እና ሌሎችም ሀገር በቀል እሴቶች፣ በምክክር እርቅንና ሰላምን የማውረድ ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡
የሀገር በቀል የምክክር መድረኮቹ አካታች እና ነፃ ናቸው፡፡
በባህላዊ የውይይት አደባባዮች ማንኛውም ዜጋ ያለ ምንም ልዩነት፣ ፍርሃትና ተፅዕኖ የራሱን ሐሳብ በነፃነት የሚገልጽባቸው መድረኮች ናቸው።
እሴቶቹ እልህንና ቂምን በይቅርታ የመስበር ጥበብ አላቸው፡፡
በሀገር በቀል ሥርዓቶች ውስጥ እንደ እርጥብ ሳር ያሉ የሰላምና የይቅርታ ምልክቶች ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡
የቱንም ያህል ለበቀል የተነሳሳ አካል ቢኖር፣ ማህበረሰቡ እነዚህን ምልክቶች ይዘው ሲማጸኑ ቂመኛው መሣሪያውን ለመጣልና ሰላምን ለመቀበል ይገደዳል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ ማነቆ እልህ፣ ትዕቢትና ያለፉ የታሪክ ቁርሾዎችን አለመርሳት ነው።
ሀገር በቀል የሰላም እሴቶቻችን የተለያዩ የፖለቲካና የብሔር ወገኖች ለሀገር መዳን ሲሉ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው፣ የጥላቻ ንግግሮችን አቁመው ወደ ይቅርታ ጠረጴዛ እንዲመጡ ትልቅ የሞራል ኃይል ይጭራሉ።
ሀገር በቀል ሕጎችና ደንቦች ሰውን ወደ ስብእናው መልሰው በሕሊና ዳኝነት ያስገድዳሉ፡፡
በሰውየው ሕሊና፣ በሞራል እና በማኅበራዊ መከባበር ላይ የተመሰረቱ ስለሆነ፡፡
ሀገር በቀል እሴቶች በሀገራዊ ምክክሩ መጨረሻ ላይ የሚደረሱ የጋራ ስምምነቶችና ውሳኔዎች በወረቀት ላይ ብቻ እንዳይቀሩ፣ የሕዝቡ የውስጥ እምነት እንዲፈጠር ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡
ሀገር በቀል እሴቶች ማኅበረሰቡ የምክክሩን ውጤቶች በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቃቸውና ለስምምነቶቹ ታማኝ እንዲሆን የውስጥ ስነ-ምግባርን ይገነባሉ።
Comments (0)
Add Comment