የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በጀርመን የተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት የሚያወግዝ “የበቃ” ወይም ‘#NoMore‘ ዘመቻ አካል የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ በጀርመን የተለያዩ ከተሞች እየተካሄ ነው።
ሰልፉ እየተካሄደ ያለው በበርሊን፣ ቦን እና ፍራንክፈርት ከተሞች ነው ተብሏል።
የበርሊኑ ሰልፍ በጀርመን መራሒተ-መንግስት መስሪያ ቤት ፊት ለፊት እየተካሄደ ሲሆን÷ ሰልፈኞቹ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በቦን በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በከተማው ዋና መቀመጫውን ያደረገው የጀርመኑ ዶቸ ቬለ የቴሌቪዥን ጣቢያ በኢትዮጵያ ላይ የሚያወጣቸው አድሏዊና የተሳሳቱ ዘገባዎች ማስተካከል እንዳለበት የሚያስገነዝቡ መልዕክቶች ተላልፈዋል ነው የተባለው፡፡
በተጨማሪም የፍራንክፈርቱ ሰልፍ መነሻውን ከሃውፕትፍሬድሆፍ አደባባይ በማድረግ በከተማው በሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ ጽህፈት ቤት የሚካሄድ ሲሆን÷ ሰልፈኞቹ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጫና የሚቃወሙ መፈክሮችን አሰምተዋል።

ከዶርትመንድ፣ ሙኒክ፣ ስቱትጋርት፣ ሌፕዚግና ሌሎች የጀርመን ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሰልፉ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በሶስቱ የጀርመን ከተሞች እየተካሄደ የሚገኘው ሰላማዊ ሰልፍ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ኤርትራውያን፣ የሌሎች አፍሪካ አገራት ዜጎችና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደተገኙም ተገልጿል።
ሰላማዊ ሰልፉን ያዘጋጀው በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ የተሰኘ ተቋም ነው።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!