ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወረራውን በመቀልበስ ያሳየውን ጀግንነት በመልሶ ግንባታው እንደሚደግመው አምናለሁ – አቶ ክርስቲያን ታደለ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት እንደመንግስት ከሚሰራቸው የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ስራዎች በተጨማሪ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገሪቱን ሊያፈርሱ የመጡ እኩይ ሃይሎችን ድል ለመንሳት ያሳየውን ጀግንነት እና አንድነት በወረራው የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍ እንደሚደግመው ጽኑ እምነት እንዳላቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የአብን ፓለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ገለፁ።
አቶ ክርስቲያን በፋና ቴሌቪዥን ስለ ኢትዮጵያ ፕሮግራም “ኅብረ ብሔራዊ ዘመቻ ለሀገር አንድነት” በሚል ርዕሰ ርዕስ በተደረገ ውይይት ላይ ተገኝተዋል።
በቆይታቸውም “አሸባሪ ቡድኑ በመላው ሀገራችን እና በህዝባችን ላይ ያደረሰው ውድመት ከ እስከ ተብሎ ሊዘረዘር የሚችል አይደለም ያሉት አቶ ክርስቲያን፥ ቡድኑ ኢትዮጵያን ማፍረስ እና ኢትዮጵያዊያንን ማዋረድ ህልሙ አድረጎ መነሳቱን አመልክተዋል።
በዚህም ለኢትዮጵያዊነት ቀናኢ አመለካከት ያላቸው የአማራ እና የአፋር ህዝቦች ላይ ያደረሰው ግፍና በደል በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም ነው ያሉት፡፡
ቡድኑ የአማራ ህዝብን ከምስረታው ጀምሮ ጠላት አድረጎ በመነሳት እና ህዝቡን ማህበራዊ እረፍት ከመንሳቱ በተጨማሪ፥ “በአማራ ህዝብ ላይ ሂሳብ አወራርዳለሁ” በሚል ስሌት ተነሳስቶ በርካታ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ውድመቶችን አድርሷል ብለዋል።
በክልሉ መሰረታዊ የሚባሉ የህዝብ አገልግሎቶች መስጫ ተቋማት በከፍተኛ ደረጃ ስለወደሙ እነዚህን ተቋማት ወደስራ ለማስፈባት እንኳን ከባድ ሁኔታ መፈጠሩንም ነው የጠቆሙት፡፡
በአማራ ክልል በሰው ህይወት፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በሀይማኖት ተቋማት እና በሌሎች በርካታ መሰረተ ልማቶች ላይ የደረሰው ውድመት የክልሉን እድገት ከ40 እሰከ 30 አመት ወደ ኋላ የሚጎትት መሆኑን አንስተዋል።
እነዚህን ውድመቶች እና በተመሳሳይ በአፋር ክልል የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እና በክልሎቹ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ቡድኑ ለእኩይ አላማው ሲያንቀሳቅሳቸው የነበሩ ተቋማት ተወርሰው ለዚሁ አላማ ሊውሉ ይገባል ብለው በግልም ሆነ እንደ አብን ድርጅት መልካም ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ አቶ ክርስቲያን ገልጸዋል፡፡
ውድመቱን በሚመለከት የሚመለከታቸው የመንግስት መስርያ ቤቶች እና ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት በገለልተኛ ሁኔታ በማጣራት ጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ በመስራት የደረሱ ጥፋቶች በወጉ ተሰንደው ለታሪክ ሊቀመጡ ይገባልም ነው ያሉት፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!