በድህረ ጦርነት የሚገጥሙ ፈተናዎችን በመቋቋም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መስራት ይገባል – አቶ እርስቱ ይርዳው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በድህረ ጦርነት የሚገጥሙ ፈተናዎችን በመቋቋም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መስራት እንደሚገባ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ገለጹ፡፡
የደቡብ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ በሀዋሳ ውይይት እያካሔዱ ነው ፡፡
በውይይት መድረኩ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ ፣ የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው በምክክር መድረኩ እንደገለጹት፥ በአገር የተፈጠረው የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ከፍ እያለ ነው።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ሰላም በመፍጠር ለመላው አለም ተምሳሌት የሆነች አገር መሆኗን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አገር እንድትሆን ይሰራል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለህዝቦች ብልጽግና መረጋገጥ መትጋት ይገባል ነው ያሉት።
ዜጎች በእርዳታ የሚኖሩባት አገር ሳትሆን በላባቸው እና በጥረታቸው ሰርተው የሚበለጽጉባት እንድትሆን አመራሩ እና መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባም አውስተዋል።
ኢትዮጵያ በውስጥ ባንዳዎች እና በውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ምክንያት ሉአላዊነቷን በመዳፈር እንደ አገር እንዳትቀጥል በሴራ ጠልፈው ሊጥሏት ሙከራ ማድረጋቸው ተነስቷል።
ይህንንም በተባበረ ክንድ የጠላትን እኩይ ሴራ ማክሸፍ መቻሉን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እና ተላላኪ መንግስት መፍጠር ያለሙ ሀይሎች አልተሳካላቸውም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ የጠላቶቻችንን አላማ ያከሸፈ ድል ተጎናጽፈናል ሲሉም ተናግረዋል።
የጠላቶቻችንን እኩይ አስተሳሰብ መላው ኢትዮጵያዊያን በጋራ መክተው ድል ከማድረግ ባለፈ የጋራ አገራዊ አንድነታችንን ለማጽናት እድል ፈጥሮልናል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የኢኮኖሚ ጦርነት ቢከፈትብንም እየተዋጋንም እየሰራንም ትልቅ ድል አስመዝግበናልም ነው ያሉት።
ጠላት ከያዛቸው ቦታዎች ጠራርገን ማስወጣት ብቻ ሳይሆን በጠላት ላይ በሁለንተናዊ መልኩ ድል መንሳት ችለናል ሲሉም ጠቁመዋል።
ተገደን በገባንበት ጦርነት የላቀ ድል ከማስመዝገብ ባለፈ ፈጥነን ወደ ልማታችን መመለስ አብይ ትኩረታችን ነው በማለት አብራርተዋል።
ጦርነት በአንድ ወገን አሸናፊነት ተደመደመ ማለት ዘላቂ ዋስትና ስለማይኖር በድህረ ጦርነት የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ አንስተዋል ።
የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት የህዝባችንን የስነ ልቦና ጉዳት በመጠገን በአዲስ መንፈስ እና አስተሳሰብ ለለውጥ መነሳሳት ይገባል ብለዋል።
ከጦርነት በኋላ ያሉ ፈተናዎችን በመቋቋም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መስራት ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ማብራራታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!