ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ባላቸው ግንኙነት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩና በድርጊታቸው የተፀፀቱ ግለሰቦች ከእስር እየተለቀቁ ነው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሽብርተኛው ህውሃት ጋር ባላቸው ልዩ ልዩ ግንኙነት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ሲጣራባቸው ከነበሩ ግለሰቦች መካከል ከፍተኛ ወንጀል ያልፈፀሙና በድርጊታቸው ተፀፅተው ይቅርታ የጠየቁ ከእስር እየተለቀቁ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ግለሰቦቹ ከእሥር ቢወጡ ለከተማዉ ስጋት የማይሆኑ መሆናቸው በጥንቃቄ ተለይተው በዋስ እንዲለቀቁ መደረጉም ተገልጿል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውን የህውሃት እና የሽብር ግብረአበሮቹን ተልዕኮ ያነገቡ ግለሰቦች ከሰላማዊ ዜጎች ጋር በመመሳሰል በህዝብ እና በሀገር ላይ የደቀኑትን ከፍተኛ ስጋት ለማስወገድ ከቡድኑ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈፀም የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በሚሰጥ መመሪያ መሰረት ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች መካከል በድርጊታቸው ተፀፅተው ይቅርታ የጠየቁትን፣ የጥፋታቸውና የተሳትፏቸው መጠን እየተለየ በዋስ ከእስር እንዲፈቱ ተደርጓል።
የተቀሩትንም እንደ ድርጊታቸው ክብደትና ቅለት እየታዬ ወደፊት እንደሚለቀቁ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በዋስ የተለቀቁ ግለሰቦች ወደፊት እንደ ጥፋታቸው በህግ እንደሚጠየቁ እና በህግ አካላት ጥሪ ሲደደረግላቸው የመቅረብ ግዴታ እንዳለባቸውም ተገልጿል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት በሽብርተኛ ከተፈረጀው ቡድን ጋር ግንኙነት ማድረግ ሆነ የሽብር ቡድኑን ዓለማ ማራመድ በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን ተረድቶ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደዳለበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ጨምሮ አስገንዝቧል።
በመጨረሻም ህብረተሰቡ የአሸባሪዎቹን እኩይ ዓላማ ተገንዝቦ ከፖሊስ ጎን በመሆን እስከአሁን መረጃና ጥቆማ በመስጠት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይም የሽብር ቡድኑን የተመለከተ መረጃ እና ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ድጋፍ የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪ አስተላልፏል፡፡