የቆዳና ቆዳ ውጤቶችን ወደ ግሪክ ለመላክ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ወደ ግሪክ ለመላክ ከባለድርሻ አካላት ጋር የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተባባሪነት በተዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ላይ ከኢትዮጵያ ቆዳ ኢንስቲትዩት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያና ግሪክ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።
በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳ÷ ኢትዮጵያ የቆዳ እና ቆዳ ውጤቶች የማቅረብ ትልቅ አቅም እንዳላት እና በዘርፉ የሚሰማራ ባለሃብት ያለውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ውጤታማ መሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የሁለቱ አገራት ባለሃብቶች የተጀመረውን ትስስር በመጠቀም በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገቡ እምነታቸው እንደሆነ መግለጻቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክትር ሙሃመድ ሁሴን በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ በዘርፉ ስላላት እምቅ ሀብት፣ በዘርፉ ስለተሰማሩ ባለሃብቶች፣ በአገሪቱ በመመረት ላይ ስለሚገኙ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ዓይነት፣ ብዛትና ጥራት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ በዘርፉ ከተሰማሩ ድርጅቶች መካከል በውይይቱ የተሳተፉት የኮልባ ታይነሪ ፒኤልሲ ሃላፊዎች÷ ድርጅታቸው ስለሚያመርታቸው ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች አይነትና ጥራት እንዲሁም ወደ ውጭ ስለሚልኳቸው ምርቶች ዝርዝር ማብራሪያና የምርታቸውን ናሙና አቅርበዋል።
በውይይቱ ከተሳተፉ የግሪክ ባለሃብቶች መካከል ቫጋሊስ ካራናሲዮስ ÷ በተደረገላቸው ገለፃና በቀረበው የምርት ናሙና መደሰታቸውን ገለጸዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!