Fana: At a Speed of Life!

በወጣቶች የሥራ እና ክህሎት ሥነ ባህሪ ላይ ያተኮረ ስትራቴጂ ጥናት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ያዘጋጀው በወጣቶች የሥራ እና ክህሎት ሥነ ባህሪ ላይ ያተኮረ ስትራቴጂ ጥናት ይፋ ሆነ፡፡
 
ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 29 የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን መሠረት በማድረግ ለአንድ ዓመት ያህል ሲዘጋጅ የቆየው ጥናት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ዴቪድ እና ሉሲ ፓካርድ ፋውንዴሽን እንዲሁም ቢቢሲ ሚዲያ አክሽን በጋራ በመተባበር አራት ክልሎችን እንደ ናሙና በመውሰድ ገጠር እና ከተማን አካቶ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
ጥናቱን ይፋ ያደረጉት በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአምስት ዓመቱ ስትራቴጂክ ዕቅዱ ላይ የሰው ሀብት ልማትን ትልቅ ትኩረት እንደሰጠው አንስተዋል፡፡
 
ይፋ የሆነው ስትራቴጂ የዕቅዱ አካል ሆኖ ወጣቶችን ማነቃቃት፣ አቅማቸውን መገንባት እንዲሁም የህይወት እና የሥራ ምርጫቸው የተሻለ እንዲሆን የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን ሥራዎችን በመስራት በስነ ባህሪ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስችልም ነው የገለጹት፡፡
 
ይፋ የሆነው ስትራቴጂ ወጣቶች መረጃ እንዲኖራቸው፣ የሰለጠኑ እና በተለያዩ አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉ እንዲሆኑ እንደሚያግዝ በመግለፅ ግቡ የጥናቱን ውጤት መሰረት በማድረግ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የወጣቶች ስነ ባህሪ ላይ በስፋት መስራት ነው ብለዋል፡፡
በዴቪድ እና ሉሲ ፓካርድ ፋውንዴሽን አማካሪ የሆኑት የምስራች በላይነህ ፥ የተዘጋጀው ስትራቴጂክ ጥናት የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሥራ እና ጤናማ ህይወት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ያመላከተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
 
በሥራ፣ በትምህርት ፣ ስነ ተዋልዶ ጤና እና ተሳታፊነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ስትራቴጂውን መሰረት ያደረጉ ስራዎችን በጋራ እንሰራለንም ነው ያሉት፡፡
 
የቢቢሲ ሚዲያ አክሽን የኢትዮጵያ ተወካይ ሚያን መሀመድ ጁኔድ በበኩላቸው ፥ በኢትዮጵያ ስነ ባህሪ ላይ የሚሰሩ ስራዎች ላይ አተኩሮ ጥናት ማድረግ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ በማስገንዘብ ፥ ሚኒስቴሩ ሚዲያዎችን በመጠቀም ወጣቶች ላይ ለሚሰራው ሥራ እና ለጥናቱ ተነሳሽነት አመስግነዋል፡፡
 
ጥናቱ በኢትዮጵያ ያሉ ለወጣቶች ከሥራ አመለካከት ጋር የተገናኙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመለወጥ መነሻ የሆኑ ግኝቶችን ማካተቱን በመርሃ ግብሩ ላይ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ዓለማቀፍ ተቋማት የተገኙ ተሳታፊዎች መናገራቸዉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.