አቶ ደመቀ መኮንን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጨት ሥራ በመጀመሩ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
በመልዕክታቸውም ፥ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ወደኋላ ያለፈባቸው የታሪክ አንጓዎች ሁሌም በደማቁ ይታወሳሉ ብለዋል፡፡
ገና ከመነሻው ፕሮጀክት “ⵝ” በሚል መነሻ ሰፊ ዝግጅት ሲደረግበት የነበረው የግንባታ ሃሳብ በይፋ መሰረት ድንጋይ ተቀምጦ ወደ ስራ ተገብቷል ፤ በሂደትም ለግንባታ ስራው ያመች ዘንድ የአባይ ወንዝ የሺህ ዓመታት ጉዞውን በጊዜያዊነት አቅጣጫው ተቀይሮ የግድቡ ግንባታ በትኩረት ሲከናወን መቆየቱን አንስተዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደትን ተከትሎ የመጀመሪያውና ሁለተኛው የሙሌት ምዕራፍ በተከታታይ መካሄዱን አንስተው ፥ ለሺህ ዓመታት ብዙ ኪሎ ሜትሮች ሲጓዝ የነበረው የአባይ ወንዝ የተወሰነው ጊዜ ብሎ “አረፍ ብሎ” ሃይል በማመንጨት ጉዞውን ቀጥሏልም ነው ያሉት፡፡
አሁን በኢትዮጵያ ህዝብ የተባበረ ድጋፍ እና ተሳትፎ፣ የባለሙያዎች ጥረት እና የአመራር ጥበብ በደረሰበት የግንባታ ደረጃ እና የቴክኖሎጂ ልማት ተርባይኑ የቅድመ ሃይል ወደ ማመንጨት መሸጋገሩን አንስተዋል፡፡
እነሆ ዛሬ ችቦው በራ! ወሳኝ እና ውስብስብ ተግባራትን ተሻግሮ እዚህ ደረጃ በቅቷልም ነው ያሉት፡፡
ለዚህ ታሪክ እውን መሆን አሻራችሁን ያሳረፋችሁ ባለሙያዎች፣ ህዝባዊ ተሳትፎውን ያስተባበራችሁ አካላት፣ በሃገር ቤት እና በውጭ የምትኖሩ መላው የኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ደስ አለችሁ፤ ደስ አለን ብለዋል፡፡
‘‘እንደጀመርነው ለዚህ አብቅተናል፤ በአጭር ጊዜ ቀሪ ስራዎችን በማጠናቀቅ ወደተሟላ ድርብርብ ድል እናሸጋግረዋለን ፤ ስናብር ስናምር! ይለዋል እንዲህ ነው!’’ ብለዋል አቶ ደመቀ፡፡
የቀደሙ አባቶቻችንን ነፃነት ከማውረስ ጀምሮ አኩሪ ታሪክ ሰርተው አልፈዋል ፤ ይህ ትውልድ ዕድለኛ ሆኖ አኩሪ ገድል ፈፅሟል ፤ ለመጪው ትውልድም ታሪካዊ መደላድሉን አኑሯም ነው ያሉት፡፡
እርግጥ ነው! ይህን አኩሪ ገድል እየሠራ ያለ ህዝብና አመራር በሌሎች አጥፊና አፍራሽ ድርጊቶች ሲፈተን ማስተዋል ግራ ማጋባቱ አይቀሬ ነውም ነው ያሉት፡፡
እንዲህ አይነት ገናና እና አኩሪ ታሪክ በሚሰራ ሃገር እና ህዝብ መሃል ሃገር የካዱ ባንዳዎች ንፁሃንን የማጥቃት እና ሃገር የማፍረስ ተልእኮ ውስጥ ተሰማርተው ማየት የእናት ሆድ ዝንጉርጉርነትን በገሃድ የሚያሳይ ነውም ብለዋል፡፡
አንዳንድ ባንዳዎችና ጨካኞች ለጊዜው ብዙ ዋጋ እያስከፈሉን ቢሆንም ፤ በሁሉም ማዕዘናት ያሉ ኢትዮጵያዊያን በየዘመኑ የሚገጥማቸውን ፈተና በድል እየተሻገሩ እንደህዳሴ ግድባችንና ሉዓላዊነትን የማስከበር ተልዕኮን በጋራ ለማስፈፀም ወደፊት እየተመሙ መጓዛቸውን ይቀጥላሉ ነው ያሉት፡፡
በግልፅ እንደሚታወቀው ከቀደሙት አባቶቻችን የወረስነው ታሪክ ይኸው ነው ፤ እኛ ደግሞ በተግባር እየሰራነው ያለው ይህንኑ የሚያፀና ነው ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ለመጪው ትውልድ ትልቅ አሻራ በማኖር በሁሉም መስክ ታላቅነታችንን የበለጠ በጋራ እውን ለማድረግ እንድንረባረብ አደራም ብለዋል፡፡
ለዚህ ድል ላበቃችሁን ሁሉ እናመሰግናለን ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክታቸውን አስፍረዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!