ታላቁ የህዳሴ ግድብ የአንድነታችን ማሳያ የዘመናችን ዳግማዊ ዓድዋ ነው – ምሁራን
አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ኃይል ለማመንጨት ከተገነባ የውሃ ቋት በላይ ለኢትዮጵያውያን እና ለኢትዮጵያ ወዳጆች የኅብረትና የአንድነት ምልክት ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ የአፍሪካ እና እስያ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ እንዳሉት ÷ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የአንድነታችን ማሳያ የዘመናችን ዳግማዊ ዓድዋ ነው ።
ግብጾች ከ25 ዓመታት በላይ የዓባይ ወንዝ ኃይል አንዳያመነጭ በግላጭም ፣ በእጃ አዙርም ሲያሴሩበት እንደነበረ አስታውሰው÷አሁን ግድቡ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ለኢትዮጵያውያን ተስፋን ያለመለመ ለቀጣይ ተግባራትም ጠንካራ የልማት ተነሳሽነትና የሞራል አቅም የገፈጠረ መሆኑን አውስተዋል።
የኢትዮ- ዓረብ ታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በበኩላቸው÷የህዳሴው ግድብ ግንበታ አሁናዊ ቁመና ከመጀመሪያው ጀምሮ በፈርኦኖች 4 ሺህ በሚደርሱ መገናኛ ብዙሃኖቻቸው፣ ከ80 ሺህ በላይ በዓለም የተበተኑ ምሁራን እና በዓባይ ወንዝ ላይ የተደረጉ ከ1 ሺህ 500 ጥናቶች በላይ በመታገዝ ከሱዳን እና ሌሎች ሀገራት ጋር በማበር የግድቡን ጉዞ ለማስተጓጎል ያደረጉት ሙከራ መክሸፉ የአንድነታችን ና ይጽናታችን ማሳያ ነው ብለዋል።
በቀጣይነት ለምናደርጋቸው ድርድሮች በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያሉንን ተወካዮቻችንን በተቻለ መጠን የዐረቡን ዓለም ስነልቡና የተገነዘቡ መሆን እንዲችሉ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል ምሁራኑ።
በየጊዜው የሚገጥሙንን ችግሮች በተረጋጋ መንገድ በንግግር እየፈታንና ሰላማችንን በማስጠበቅ ለሜጋ ፕሮጀክቶቻችን የምናደርገውን ድጋፍ መቀጠልም ይኖርብናልም ነው ያሉት።
በአፈወርቅ አለሙ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!