በቅርቡ ለሚጀመረው የ ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ግብዓት የሚሆን ውይይት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይፋ ለሚደረገው የ ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ግብዓት የሚሆን ውይይት በድሬዳዋ መዘጋጀቱን ሚኒስትር ዴኤታው ሺሰማ ገብረ ሥላሴ አስታወቁ።
ውይይቱ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ብሎም የዘርፉን ልማት ለመደገፍ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡
የ ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ምክክር ተደርጎበት ወደ ሥራ ሲገባ፥ ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ውስጥ ምርት እድገት (ጂ ዲ ፒ) እያበረከቱት ያሉትን አስተዋፅኦ እንደሚያሳድግ ከወዲሁ ተሥፋ እንደተጣለበትም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡
ኢንዱስትሪዎች ከሥራ እድል ፈጠራ፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረት አንጻር ሊጫወቱት የሚገባው ሚና የጎላ እንዲሆን ቢጠበቅም ፥ በተለያዩ ምክንያቶች ውጤታማ አለመሆናቸውን አቶ ሺሰማህ ተናግረዋል፡፡
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታትና የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የኢንዱስትሪ ሽግግር ለማድረግ የሚያስችሉ ሂደት ላይ በማተኮር እየገጠሙ ያሉ የፋይናንስ፣ የገበያና የአቅም ግንባታ ክፍተቶችን በመለየት ድጋፍ ይደረጋልም ነው ያሉት።
የድሬዳዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡኽ በበኩላቸው፥ ድሬዳዋን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አመላክተዋል።
በቀጣይም በአስተዳደሩ የሚገኙትን አነስተኛ፣ መካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ለሀገራዊ ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ድሬዳዋ ለጅቡቲ ወደብ ቅርብ መሆኗ፣የአየርና የየብስ ትራንስፖርት ከሞላ ጎደል የተሟላ መሆኑና ሌሎች መሠረተ ልማቶች በበቂ መጠን እንደመገኘታቸው ለዘርፉ ምቹና ተመራጭ ያደርጋታልም ብለዋል፡፡
በእዮናዳብ አንዱዓለም