Fana: At a Speed of Life!

በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመመለስ እየተሠራ ነው – አምባሳደር ሌንጮ ባቲ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ ዓረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አገራቸው ለመመለስ ከአገሪቱ መንግሥት ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑን በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ለኢፕድ እደገለጹት÷ በተለያየ ምክንያት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ገብተው ለእስርና ለእንግልት የተዳረጉ ኢትዮጵያውያንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አገራቸው ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየሠራ ነው።

ከሳዑዲ የሚመለሱ ዜጎችን በተመለከተ ከተመለሱ በኋላ ችግር ላይ እንዳይወድቁ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከክልሎች ጋር ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።

በእሳቸው የሚመራው በሳዑዲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሠራተኞችን ያካተተው ኮሚቴም÷ በጉዳዩ ዙሪያ ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና የሳዑዲ ዓረቢያ ግንኙነት ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ግንኙነት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ለሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ፣ ለትምህርትና በሥራ ምክንያት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ጉዞ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያወሱት አምባሳደሩ÷ አሁንም በሳዑዲ ዓረቢያ ለእስራትና ለእንግልት የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን ለተመሳሳይ ዓላማ ከአዲስ አበባ እስከ ሳዑዲና የመን ድረስ ኔትወርክ በዘረጉ ደላላዎች ተታልለው በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ እየገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለዜጎቻችን እስራት መነሻ የሆነው በንጉስ ሳልማን ቢን አብደልአዚዝ የሚመራው አዲሱ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት አገሪቱን ለማዘመን ብሎም በርካታ የሥራ ዘርፎች በሳዑዲ ዜጎች እንዲሸፈን አዲስ ራዕይ ይዘው መምጣታቸው ነው ያሉት አምባሳደሩ÷ ከሌሎች አገራት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚሄዱ ሠራተኞች በሕግ አግባብ በተሟላ ሰነድ ብቻ በአገሪቱ መሥራት አለባቸው የሚል ገደብ በመቀመጡ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በብዙ ውጥረት ውስጥ ሆኖ ከሳዑዲ መንግሥት ጋር በመነጋገር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 42 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን ወደ አገር ቤት መመለሱን አምባሳደሩ አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም ዜጎቻችን ወደ አገራቸው እስኪመለሱ ድረስ የሳዑዲ መንግሥት የዓለም አቀፉን የእስረኞች አያያዝ መብትን በማክበር በእስር ቤት ቆይታቸው አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ኤምባሲው በቅርበት እየተከታተለ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሕጋዊ መንገድ ወደ ሳዑዲ ለመሄድ ተመዝግበው ነገር ግን የተፈጠረውን ችግር ፈርተው የቀሩ ወገኖችም መሄድ እንደሚችሉ አምባሳደር ሌንጮ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ÷ አንዳንድ ዜጎች ፓስፖርት የሌላቸው መሆናቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለመቻሉ እንዲሁም የሰለጠኑ ገዳዮች ከዜጎች ጋር ተቀላቅለው እንዳይገቡ ጥርጣሬ መኖሩን በሳዑዲ ዓረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ማነቆ ሆነዋል፡፡

በከፍተኛ ጥንቃቄ ኢትዮጵያውያንን ግን ወደ አገራቸው ለመመለስ በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ማብራራታቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.