Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ከ13 ቢሊየን ብር በላይ በጀት የመስኖ ግድቦች ግንባታ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ግብርናውን ከዝናብ ጠባቂነት ለማላቀቅ ከ13 ቢሊየን ብር በላይ በጀት መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ግድቦች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊስ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋና የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ዛሬ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ጭቋላና ወንጂ ኩሩፍቱ በበጋ መስኖ የለማውን የስንዴ ማሳ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ እንደገለጹት፤ ለበጋ መስኖ ልማት 20 ሺህ የሚጠጉ ከፍተኛ ጉልበት ያላቸውና መካከለኛ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሮች ተከፋፍለዋል።

በክልሉ ሁሉም ዞኖች ከ355 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ እያለማን ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፤ ተጨማሪ 270 ሺህ ሄክታር መሬት ለዘር ዝግጁ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በሚቀጥለው ዓመት 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ዕቅድ መያዙን ጠቁመው፤ ለዚህም የመስኖ ግድቦች ግንባታና የጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ግብርናውን ከዝናብ ጠባቂነት ለማላቀቅ ከ13 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ወጪ መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ልማት ግድቦችን እየገነባን ነው ብለዋል ።

በዚህም በቀጣይ አራት ዓመታት የክልሉን ግብርና ከዝናብ ጠባቂነት በማላቀቅ በመስኖ የሚለማው መሬት እስከ 4 ሚሊየን ሄክታር ለማድረስ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው፤ በኦሮሚያ ክልል በግብርና ሴክተር እየተመዘገበ ያለው ውጤት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ አርሶ አደሩ የውሃ መሳቢያ ሞተር፣ የመካናይዜሽን አገልግሎትና የገበያ ትስስር ተደራሽ ለማድረግ የገጠር ፋይናንስ አሰራር እየዘረጋን ነው ብለዋል ።

በምስራቅ፣ ደቡብ ምዕራብና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች የመስኖ ስንዴ ልማት በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መመልከታቸውንና ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር በመፍጠር የልፋቱን ዋጋ እንዲያገኝ መደረግ እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊስ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ አርሶ አደሩ ያለበትን የውሃ እጥረት ለመፍታት አምራቹን ያሳተፈ የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ አነስተኛና መካክለኛ ግድቦች ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

የገጠር ፋይናንስ ተደራሽነትን ማረጋገጥ በቀጣይ የሚሰራበት መሆኑንም ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.