በአፋር ክልል በቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ተጎበኙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ በቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የተከናወኑ የልማት ስራዎች በፕሮጀክቱ አመራሮች ተጎብኝተዋል፡፡
የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በአፋር ክልል ተግባራዊ ከሚደረግባቸው ወረዳዎች የአሚባራ ወረዳ አንዱ ነው ተብሏል።
ፕሮጀቱ በርካታ የልማት ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የተጠቀሰ ሲሆን÷ በፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ደረሳ አሊ የተመራ ቡድን በአሚባራ ወረዳ በመገኘት የፕሮጀክቱን የእቅድ አፈጻጸምና የተሰሩ ስራዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
ባለፈው በጀት ዓመት በአሚባራ ወረዳ፣ በዱልዓሌና ሲድሃፋጌ ቀበሌዎች በ25 ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት መኖ ማልማት የተቻለ ሲሆን÷ ሁለተኛ ዙር የምርት መሰብሰብ ስራ እየተከናወነ ይገኛልም ነው የተባለው።
በአዳብቶሌ ከተማ የተጀመረው የመኖ ማከማቻ መጋዘን ግንባታም ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት መመልከት ተችሏል።
በ2014 በጀት ዓመት በአሚባራ ወረዳ በ100 ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት መኖ በስፋት ለማልማት ታቅዶ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን በጉብኝቱ ወቅት አቶ ደረሳ አሊ መግለጻቻን ከአፋር ክልል ቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡