በተሽከርካሪ እና እሳት አደጋ የ1 ሰው ህይወት ሲያልፍ 230 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ትናንት ምሽት በተከሰተ የተሽከርካሪ እና የእሳት አደጋ የ1 ሰው ህይወት ሲያልፍ 230 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት መውደሙ ተገለፀ፡፡
የመኪና አደጋው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ትናንት ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ14 ደቂቃ የደረሰ ሲሆን ÷ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ አንድ ግሮሰሪ ውስጥ ጥሶ በመግባት ባደረገሰው አደጋ የ1 ሰው ህይወት አልፏል።
ከዚህ ባለፈም 4 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ማድረሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም መላካቸው ተገልጿል፡፡
በዚህ አካባቢ በተደጋጋሚ የተሽከርካሪ አደጋ የሚደርስ በመሆኑ አሽከርካሪዎች በሚያሽከረክሩበት ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል ትናንት ምሽት 1 ሰዓት ከ4 ደቂቃ በአዲስ አበባ ከተማ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ገርጂ ኖክ ማደያ 40/60 ኮንዶሚኒየም 13ኛ ፎቅ ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውሉ ዕቃዎች ማስቀመጫ ክፍል ውስጥ በደረሰ የእሳት አደጋ 200 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 2 ጭላሎ ሆቴል ጀርባ በ3 ቤቶች ላይ በተከሰተ የእሳት አደጋ የ30 ሺህ ብር ንብረት ውድመት መድረሱ የተገለፀ ሲሆን፥ አደጋውን ለመቆጣጥር በተደረገ ርብርብ በቦታው እና በአካባቢው ሊወድም ይችል የነበረን የ4 ሚሊየን ብር ንብረት ማዳን መቻሉን ተገልጿል።