አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የሩሲያ፣ የአውስትራሊያ እና የአርመንያ አምባሳደሮችን ጋር ተወያይተዋል።
በዚህ ወቅትም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ኢትዮጵያ ከሶስቱም ሀገራት ጋር ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ያላት መሆኑን አውስተዋል።
ግንኙነቱን በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በባህል፣ በትምህርት፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ከሀገራቱ ጋር ከዚህ በፊት የተፈረሙ ስምምነቶችን ወደ ተግባር በመለወጥ አዳዲስ ስምምነቶችን ለመፈራረም እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እንደምትሰራ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የሩሲያ፣ የአውስትራሊያ እና የአርመንያ አምባሳደሮች በበኩላቸው በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለውን ኢኮኖሚዊ እና ፖለቲካዊ ለውጥ አድንቀዋል።
ከዚህ ቀደም የተፈረሙ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ከመለወጥ ባለፈ አዳዲስ ስምምነቶችን በመፈራረም የሚጠበቀባችውን ለማከናወን በትኩረት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።