Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ ኤች አር 6600 ረቂቅን ኮንግረሱ በምንም መልኩ መደገፍ የለበትም ሲል ቅሬታውን አሰማ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት ኤች አር 6600 ረቂቅን ኮንግረሱ በምንም መልኩ መደገፍ የለበትም ሲል ቅሬታውን አሰማ፡፡

በአፕ ስቴት ኒውዮርክ ኮንግረስማን ጆሴፍ ሞራለ ቡድን ጋር በተደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ነው የምክር ቤቱ አባላት በረቂቁ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ያሰሙት።

በስብሰባው ወቅትም የኒውዮርክና አካባቢው የዜጎች ምክር ቤት ኢትዮጵያ አሜሪካውያን መራጮች በዴሞክራት ፓርቲ አካሄድ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ ለተወካዩ ጆሴፍ ሞራለ ፥ ኤች አር ኢ ኤስ128 ህግን ስናሳልፍ ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ ያደረገውን መጠነ ሰፊ በደልና ወንጀል በማመዛዘን የደገፋችሁን እና ህጉንም እንዲወጣ የረዳችሁን ባለስልጣናት መልሳችሁ ይህንን የሚያፈርስ ረቂቅ ህግ ማውጣታችሁ እጅግ የሚያሳዝን ነው ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን በማዕቀብ ለመምታት የሚደረገው ሩጫ ተገቢና ትክክል ባለመሆኑ እንዲያስቆሙልን እንጠይቃለን ሲሉም ለኮንግረሱ ተወካይ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር በረቂቅ ህጉ አዝነዋል ይህ የምክር ቤቱ ቀዳሚ አጀንዳና ጥቅም በመሆኑ ድጋፍ እንፈልጋለን በማለት የተናገሩት ደግሞ የምክር ቤቱ አመራር እና የዩኒቲ ፎር ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ስዩም አሰፋ ናቸው።

የኮንግረሱ ወኪል ቢሯቸው ኤች አር 6600 የተባለውን ረቂቅ ህግ በጥልቀት እንደሚመረምሩት እና ሴኔት ላይ ያለውን ተመሳሳይ ረቂቅም በማጥናት የምክር ቤቱን ስጋት በመረዳት አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ እርምጃው ምን እንደሚሆን በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል ።

ዲያቆን ዮሴፍ አያይዘውም በረቂቅ ህጉ ላይ የተነሱት አንዳንዶቹ ስጋቶች ያለፉባቸውና መንግስት የሰላምን ዋጋ በማገናዘብ የወሰዳቸው እርምጃዎች መኖራቸውን አንስተው አብራርተዋል።

ረቂቅ ህጉን በማፅደቅ በህዝብ ላይ ኢኮኖሚያዊ ችግር ከመድረሱ በፊት በአስቸኳይ ትብብርዎን እንፈልጋለን በማለት ጠይቀዋል።

ኮንግረስማኑ በቅርቡ መልስ እንደሚሰጡ በመጥቀስ ስብሰባው የተጠናቀቀ ሲሆን ፥ በቀጣይ ሳምንት ከሌሎች ኮንግረሶች ጋር ተመሳሳይ ስብሰባ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት እንደሚያደርግ ተነስቷል።

የኢትዮጵያውያን አሜሪካ የዜጎች ምክር ቤት በተደጋጋሚ ከአሜሪካ ምክርቤት እና ሴኔት ጋር እያደረገ ያለውን የዲፕሎማሲ ጫና አጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል፡፡

በዚህም ምክር ቤቱ ያዘጋጀውን ረቂቅ ህጉን የሚቃወም እንቅስቃሴ ፊርማቸውን በመፈረም እንቅስቃሴውን ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲደግፉ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ አምሳሉ ካሳው ጥሪ ማቅረባቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.