በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመራጭ ተመራጭ ትስስር ይፋዊ የስራ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመራጭ ተመራጭ ትስስር ይፋዊ የስራ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ተካሄደ።
በመርሀ ግብሩ ላይ ከንቲባዋ ለንግድ ሥራ 63 ሼዶችንና ለከተማ ግብርና የሚሆኑ 271 የመስሪያ ቦታ ለወጣቶች አስረክበዋል፡፡
የመራጭ ተመራጭ ትስስር በይፋ የተጀመረ ሲሆን÷ በክፍለ ከተማው ተወዳድረው በህዝብ የተመረጡት ከንቲባ አዳነችን ጨምሮ ሌሎች በህዝብ የተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመድረኩ እንደገለጹት÷ በሕልውና ትግሉ ላይ በጋራ ሰርተን ውጤት እንዳስመዘገበነው ሁሉ በሌሎች የልማት ሥራዎችም ድላችንን ለመድገምና የመረጠንን ሕዝብ ለመካስ እንዲቻል በጋራ እየተደጋገፍን እና እየተመካከርን መሥራት ይኖርብናል ብለዋል።
በምርጫ ወቅት ከመረጣችሁን ቃላችንን ጠብቀን እናገለግላችሏለን ብለን ቃል ገብተን ነበር ያሉት ከንቲባዋ÷ ቃላችንን ምንጊዜም ቢሆን አናጥፈውም፣ እናገለግላችኋለን ብለዋል፡፡
የብልጽግና ጉባኤ የወሰናቸውን ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች አስመልክቶ ከህዝብ ጋር ውይይት እንደሚደረግ ጠቅሰው÷ ህዝቡ እንድናስተካክል እንድናርም የሚፈልገውም ነገር ካለ ፊት ለፊት እንነጋገራለን ብለዋል፡፡
ትውልዱ የላቀ ስብዕና መላበስ እንዳለበት፣ የፖለቲካ ልዩነት በመድረክና በሰለጠነ መንገድ መስተናገድ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የሚዋቀረው የትስስር ኮሚቴ የመራጭ ተመራጭ ቀጥተኛ ግንኙነት መፍጠር ላይ በትኩረት በመስራት የህዝብን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል አደረጃጀት ነው ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር ናቸው፡፡
በስነ-ስርዓቱ ላይ የኑሮ ጫና ላለባቸው ወገኖችም የማዕድ ማጋራት መርሀ ግብር መከናወኑን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!